ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ ነው!

17

ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ግንቦት 30/1933 ዓ.ም አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመጀመሪያ እትሙን የጀመረበት ዕለት ነው። የጋዜጣው የተቋቋመው ኢትዮጵያን ለአምስት ዓመታት የያዘችው ጣሊያን ከተሸነፈች በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከስደት ከተመለሱ ከአንድ ወር በኋላ ነበር።

የጋዜጣው ስም ንጉሠ ነገሥቱ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ከተናገሩት ንግግር ጋር የተያያዘ ነው። በንግግራቸውም “ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ ነው” ብለው ነበር።

የመጀመሪያው እትም የንጉሠ ነገሥቱን አዲስ አበባ መግባት የሚያሳይ ትልቅ ፎቶ የያዘ ሲኾን ዋናው ርዕስ ደግሞ “የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መጀመር” የሚል ነበር። የጋዜጣው መክፈቻ አንቀጽ ለመላው ኢትዮጵያውያን ለመሥራት እንደተመሠረተ ገልጿል።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ የተመሠረተው “ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ለሀገር እና ለሕዝብ ጥቅም የሚያስፈልገውን ሁሉ እየጠቆመ፣ ሕዝብ ለሀገሩ፣ ለመሪው እና ለመንግሥቱ ማድረግ የሚገባውን እያብራራ፣ የበጎን ሥራ መንገድ የሚመራ” እንዲኾን ነው።

ጋዜጣውም በ“እውነት፣ ረዳትነት እና አገልግሎት” በሚሉት ሦስት መሠረታዊ ቃላት ሥራውን እንደሚሠራ አሳውቋል።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከ1933 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ለ84 ዓመታት ያህል ህትመቱ ሳይቋረጥ በአማርኛ ቋንቋ እየታተመ ቀጥሏል። በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን በቀን 10 ሺህ ቅጂዎች ይታተም የነበረ ሲኾን፣ 60ኛ ዓመቱን በ1993 ዓ.ም ሲያከብር ዕለታዊ ህትመቱ 40 ሺህ ደርሶ ነበር። ጋዜጣው አሁን ላይ የይዘት እና የቅርጽ ለውጥ በማድረግ በልዩ አቀራረብ ጉዞውን ቀጥሏል። ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ 60ኛ ዓመት ልዩ ዕትም

✍”ጋዜጠኝነትስ እንደ ጳውሎስ!”

ጳውሎስ ኞኞ ከኅዳር 11/1926 ዓ.ም እስከ 1984 ዓ.ም በኖረባቸው ዓመታት በርካታ ከመቃብር በላይ ስሙን የሚያስጠሩ ሥራዎችን አከናውኗል። ጳውሎስ ኞኞ ታዋቂ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ጸሐፌ ተውኔት፣ ሰዓሊ እና የታሪክ ጸሐፊም ነበር። በትምህርት ብዙም ባይገፋም፣ በተፈጥሮ የታደለው የመመርመር እና የመጻፍ ችሎታው በጋዜጠኝነት ሙያ በዘመኑ ግንባር ቀደም የነበር ነው።

በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና በኢትዮጵያ ራዲዮ ሠርቷል። በርካታ መጻሕፍትን እና ትያትሮችን የጻፈ ሲኾን፣ ከእነዚህም የሴቶች አምባ፣ አጤ ምኒልክ፣ አጤ ቴዎድሮስ እና አስደናቂ ታሪኮች ይጠቀሳሉ።

ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱስን በተለይም በዚህ ክፍል ውስጥ ያለውን የሐዋርያው ጳውሎስን መልዕክት አድናቂ የነበረ ሲኾን በዚህም ምክንያት ልጁን “ሐዋርያው” ብሎ እንደጠራው ይነገርለታል።

መንገድ ላይ ወድቃ የሚያገኛትን ወረቀት ሁሉ ማንበብ ልማዱ ነበር። ግልጽነት፣ ድፍረት፣ ለወገን ደራሽነት እና ጨዋነት ከባህሪያቱ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ለፕሬስ ነጻነት በጽኑ ይሟገት የነበረ ሲኾን ይህ ተጋድሎው ለእንግልት ዳርጎታል።

ጳውሎስ ለድርቅ እና ርሀብ ተጠቂዎች እንዲሁም ጠያቂ እና ዘመድ ለሌላቸው ሰዎች ደራሽ ነበር ይባልለታል። የትዳር አጋሩን እና ትዳሩን አክባሪ፣ ለታሪክ እና ለባሕል ተቆርቋሪ፣ ለማኅበራዊ ሕይወት ትኩረት የሚሰጥ ሰው ነበር። የዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ አድናቂ እንደነበርም ነው የሚነገረው።

ጳውሎስ ኞኞ በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ “ጋዜጠኝነትስ እንደ ጳውሎስ!” የተባለለት ታላቅ ሰው ነው።

ምንጭ ደረጄ ትዕዛዙ ከጻፉት “ጳውሎስ ኞኞ ከ1926-1984” የተሰኘ መጽሐፍ

✍“ሀ..ሁ… ዕውቀት ይስፋ፣ ድንቁርና ይጥፋ – ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ”

ከዕፅዋት ቀለም አንጥረው፣ ከሸምበቆ ብዕር ቀርጸው፣ የፍየል ቆዳ ፍቀው እና አለስልሰው በመጽሐፍ “ሀ..ሁ… ዕውቀት ይስፋ፣ ድንቁርና ይጥፋ – ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” የሚል መፈክር ተጠቅመው ወደ ማኅበረሰቡ ያዘለቁት “የፊደል ገበታው ጌታ” ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሔረ-ቡልጋ የተወለዱት ሰሜን ሸዋ ቡልጋ ክታብ ወይራ አክርሚት በተባለ ቀበሌ ነው፡፡

ከአባታቸው ከመምህር ገብረ ሥላሴ ቢልልኝ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሥዕለ ሚካኤል ወልደ አብ ታኅሣሥ 24/1895 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡ “የፊደል ገበታ አባት” በሚል የሚጠሩት እኝህ ሰው በመጀመሪያ በብራና ላይ በእጃቸው እየጻፉ፣ በመቀጠልም በማተሚያ ቤት ማሽን እያባዙ ለሕዝብ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡

ተስፋ ገብረ ሥላሴ በ1909 ዓ.ም የ15 ዓመት ልጅ ኾነው ከትውልድ መንደራቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ያረፉበት መንደር አራት ኪሎ ነበር፡፡

የተስፋ ገብረ ሥላሴን የሥራ እና የሕይዎት ታሪክን ማዕከል አድርጎ የሀገሪቱን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባሕላዊ ጉዳዮች በስፋት የሚያስስ “ዘመን ተሻጋሪ ባለውለታ” መጽሐፍ ተስፋ ገብረ ሥላሴ የሕዝብ እና የሀገር ባለውለታ መኾን የቻሉት በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው እንደኾነ ይገልጻል፡፡

ከኢጣሊያ ወረራ በፊት እና በኋላም ለእስር እና ውንጀላ ተዳርገዋል። በመጨረሻ ሁሉንም አሸንፈው በተደጋጋሚ ተሸላሚ ኾነዋል፡፡ በአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የቀኝ አዝማች ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበርም ሥራቸውን ከትቦ ደጋግሞ አመሥግኗቸዋል፡፡

ግንቦት 26/1992 ዓ.ም ‹‹የፊደል ገበታ አባት›› በመባል የሚታወቁት ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ (ዘብሔረ ቡልጋ) ያረፉበት ዕለት ነው።

✍የኤድስ ወረርሽኝ!

ግንቦት 28/1981 ለዓለማችን እስካሁን ስጋት ኾኖ የቀጠለው የኤድስ በሽታ የታወቀበት ዕለት ነበር። ይህ ዓለማችንን እጅግ የፈተነው የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል (CDC) ምንነቱን የለየው የኤድስ ወረርሽኝ አሁንም ድረስ ውሉ ያልተገኘለት በሽታ ኾኖ ቀጥሏል። ይህ በሽታ በአሜሪካ በሎስ አንጀለስ የሚኖሩ አምስት ወጣት ሰዎች ላይ በተደረገ ምርመራ ነበር መታወቅ የቻለው።

በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ከተለየ እና ዓለም እንዲከላከለው ከታወጀ በኋላም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ እና በመላው ዓለም ያሉ ማኅበረሰቦችን በእጅጉ የጎዳ ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ ኾኖ ዛሬም እንደቀጠለ ነው።

የኤች አይ ቪ ኤድስ በኢትዮጵያ የታወቀው በ1984 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገ ምርመራ እንደኾነ ታሪክ ይነግረናል። ኤች አይ ቪ ኤድስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በይፋ መታወቁን ተከትሎ ብዙም ሳይቆይ ተከስቶ ብዙ ጉዳቶችን አስከትሏል፤ አሁንም ድረስ ጉዳቱ ቀጥሏል።

በ1980ዎቹ መጨረሻ እና በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በተለይም በትላልቅ የንግድ መስመሮች ላይ በሚገኙ ከተሞች እና ከፍተኛ ተጋላጭነት ባላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ቫይረሱ በፍጥነት መስፋፋት እንዳሳየም ነው መረጃው የሚጠቁመው።

የኤች አይ ቪ ስርጭት በኢትዮጵያ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ዝቅተኛ የነበረ ቢኾንም በ1990ዎቹ ውስጥ ግን በከፍተኛ ፍጥነት ጨምሯል፤ ይህም ኤድስ በአዋቂዎች ዘንድ ዋነኛው የሕመም እና የሞት መንስኤ እንዲኾን አድርጎታል። ይህ በሽታ ዛሬም ሰዎችን እየጎዳ የሚገኝ በመኾኑ ጥንቃቄ ያሻዋል። ምንጭ፦ ሲዲሲ(CDC)

ዘጋቢ: ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለሰላም የተዘረጉ እጆች፤ ሰላምን የሰበኩ አንደበቶች”
Next articleከፍተኛ መሪዎች በአዲስ ዘመን ከተማ አሥተዳደር የተገነባውን ትምህርት ቤት መርቀው ሥራ አስጀመሩ።