“ለሰላም የተዘረጉ እጆች፤ ሰላምን የሰበኩ አንደበቶች”

35

ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እጆች ለሰላም ተዘርግተዋል፣ አንደበቶች ሰላምን ሰብከዋል። እናቶች በእንባ እየታጀቡ ስለ ሰላም ጮኸዋል። አባቶች ሳግ እየተናነቃቸው ሰላምን ተጣርተዋል። ሕጻናት ሰላምን ተመኝተዋል። ወጣቶች ሰላምን ሽተዋል። አረጋውያን ስለ ሰላም ተማጽነዋል። ደጋጎቹ ለሰላም ጸልየዋል።

ተራራዎች፣ ሜዳዎች፣ ሸለቆዎች፣ ሸንተረሮች የጥይትን ድምጽ ሰልችተዋል። ሰላምን ናፍቀዋል። ላምና በሬዎቻቸውን ይዘው በሜዳ ላይ የሚሰባበሱት እረኞች፣ የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል የአንበሳ ደቦል በሜዳ ሙሉ የሚዛለሉ ልጆች፣ በዛፍ ስር ተቀምጠው የሚመካከሩ ሽማግሌዎች፣ እንሥራ አዝለው ወደ ምንጭ የሚወርዱ ልጃገረዶች እና እናቶች “የሰላም ያለህ” ብለዋል።

ሰላም በሌለ ጊዜ እረኞች ከብቶቻቸውን ይዘው በሰላም አይሰባሰቡም። ሰላም በሌለ ጊዜ ልጆች በደስታ አይቦርቁም። ወደ ሜዳም አይዘልቁም። ሰላም ከሌለ እናቶች አይስቁም። አባቶች በደስታ አይመርቁም። ሁሉም ያስጨንቃል፤ ያሳቅቃልና።

ሰላም ከሌለ የሀገሬው ሰው ከጓሮው እሸት፣ ከማጀት ወተት አያገኝም። ጓሮዎች ጦም ያድራሉ። የወተት ማለቢያ ግሬራዎች ባዶ ይኾናሉ። ላሞችም ወተት ይነጥፋሉ። በሬዎችም ከቀንበር ተለይተው ይባጃሉ። አፈር ገፍተው ሀገሬውን የሚያጠግቡ ብርቱ ገበሬዎች ቀንበር ይሰቅላሉ። በሬ እና ገበሬ ይለያያሉ። ያን ጊዜ የከፋው መከራ ይመጣል።

ሰላም ከሌለ ነጋዴዎች የብሱን አቋርጠው፣ ባሕሩን ሰንጥቀው ሸቀጥ ይዘው ወደ ቀዬው አይዘልቁም። ለንግድ አይወጡም። ቢወጡም አይመለሱም።

እነኾ ሰላም የናፈቀቻቸው አልፍ አዕላፍ ወገኖች የሰላም ያለህ እያሉ ወደ ዓደባባይ ወጥተዋል። የሰላም ያለህ እያሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጮኸዋል። ሰላምን ይቀበሏት ዘንድ እጃቸውን ዘርግተዋል። ልባቸውን ለሰላም አዘጋጅተዋል። ለሰላምም አስገዝተዋል።

በደል በጽዋው አልፎ ፈስስሷል። በተወለዱበት ቀዬ ቸር አውሎኝ ብሎ መዋል፣ ቸር አሳድረኝ ብሎ በሰላም ማደር እንደብርቅ ኾኖ ከርሟል። ከአውራጃ ወደ አውራጃ በሰላም መመላለስ ብርቅ ኾኗል። በሰላም ወጥቶ መግባት እንደ ድንቅ ተቆጥሯል። ልጆች ወላጆቻቸውን አልቀበሩም። ወላጆች ልጆቻቸውን አልዳሩም። በሀዘን እና በደስታው ሁሉ የሚገናኙት ተለያይተዋል። በሩቅ ኾነው ከተነፋፈቁ ጊዜያት ተቆጥረዋል።

ገበሬዎች በላሞቻቸው አያዝዙባቸውም፣ በበሬዎቻቸው መብት የላቸውም። በፍየል እና በጎቻቸውም የመወሰን ሥልጣን አልተሰጣቸውም። የደረሰ ሁሉ ጎትቶ ያርዳቸዋል። ያገኘ ሁሉ ይሸጣቸዋል፣ ይለውጣቸዋል እንጂ።

እኒያ በዱር በገደል ተንከራትተው ያረቧቸውን በግና ፍየሎቻቸው ለምን ታረዱ ብለው በጠየቁ ጊዜ የሚያዳፋቸው፣ የሚገፋቸው፣ የሚገርፋቸው ብዙ ነው። እንደ ልጆቻቸው እየሳሱ ያሳደጓቸውን በሬዎች ሲበሉባቸው፣ ከአውሬ ጠብቀው ያኖሯቸውን በግ እና ፍየሎች ሲታረዱባቸው አዝነዋል። አንብተዋል። “አቤቱ አምላክ ኾይ” መልካሙን ቀን አምጣ እያሉ አምላካቸውን ተማጽነዋል። ቀዬው ሰላም የሚኾንብት፣ በሰላም ተወጥቶ የሚገባበት፣ በማሳው ሁሉ ጅራፍ እንጂ ጥይት የማይጮህበት፣ እናት እና ልጅ የማይለያዩበት፣ ንጹሐን የማይገደሉበት፣ ሰዎች እንደ እንስሳት በዋጋ የማይተመኑበት ዘመን ይመጣ ዘንድ አብዝተው ተማጽነዋል።

ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው ክብር ሲሉ በዱር በገደል የሚንከራተቱ ጀግኖች ደግሞ ሰላምን ከሚያውኩት ጋር ተጋፍጥጠዋል። እነርሱ እየወደቁ ብዙዎችን አቁመዋል። እነርሱ እየደሙ ሌሎችን አክመዋል። እነርሱ እየሞቱ ሌሎችን አኑረዋል። እነርሱ እየተራቡ ሌሎችን አጥግበዋል። እነርሱ እየተጠሙ ሌሎችን አጠጥተዋል። እነርሱ እንቅልፍ አጥተው ሌሎቹ እንዲያርፉ አድርገዋል።

በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ንጹሐን እየታፈኑ ለገበያ ወጥተዋል፣ በገንዘብ ተተምነዋል። የተተመነላቸውን ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ እንደ ወጡ ቀርተዋል። በዱር በገደል የአውሬ ቀለብ ኾነዋል።

ባለ ተስፋ ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ርቀዋል። ትውልድ ገንቢ መምህራን ተገድለዋል። ዝናብ የሚያፍራቸው፣ ሀገር የሚያከብራቸው፣ ወንዝ የሚቆምላቸው የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተዋርደዋል። የግፍ ጽዋ ተጎንጭተዋል። በግፍ እንደ እንስሳት ተጎንብሰው ድኸዋል። በሰቀቀንም ተገድለዋል።

“ነጻ እናወጣሃለን” በምትል መከለያ ነፍጥ ያነሱ ታጣቂዎች ለዘመናት አጥብቆ ይዘውት የኖሩትን፣ ከአያት ቅድመ አያት የተቀበሉትን ነጻነት አሳጧቸው፣ የመከራ ማዕት አወረዱባቸው። ባዕዳን ያልደፈሯቸውን ወገኖቻቸውን አሰቃዩዋቸው።

ከዛሬ ነገ ይሻላል እያለ አንገቱን ደፍቶ የኖረው፣ አብዝቶ የታገሰው፣ ሊጎርሳት የጠቀለላትን እንጀራ ሳይቀር ሲነጠቅ የባጀው የሀገሬው ሰው አሁን ግን በቃኝ ብሏል። ዝምታውን ሰብሯል። ትዕግሥትቱን ፈጽሟል። በቃኝ ብሎ ተነስቷል። ሰላምን እየሰበከ ወደ አደባባይ ወጥቷል። የበደልም ልክ አለው፣ የትዕግስትም ወሰን አለው እያለ ተነስቷል።

ከሰሞኑ በበጌምድር ወረዳዎች ተመላልሻለሁ። በሰላም እጦት ውስጥ ከኖረው የሀገሬው ሰው ጋር ባጅቻለሁ። ከእግራቸው ሥር ተቀምጬ ስለ አከራረማቸው ጠይቄያለሁ። ስለ አኗኗራቸው ከአንደበታቸው ሰምቻለሁ። ስሜታቸውንም አድምጫለሁ።

ከማማው ደብረ ታቦር – ነፋስ መውጫ- ላይ ጋይንት- ታች ጋይንት- እስቴ- አንዳቤት ድረስ ተጉዣለሁ። የሁሉንም ስሜት የመስማት እድል አግኝቻለሁ። ሁሉም እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መስካሪ መከራ በቃን እያሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል። በኅብረት እየወጡ ስለ ሰላም መክረዋል። ስለ ሰላም ሰብከዋል።
በዘመናችን እንዲህ ዓይነት በደል አይተን አናውቅም ብለዋል።

ሰው በደል፣ ከብት ገደል አይወድምና ከዚህ በላይ በደል ይበቃናል። የተሸከምንበት ትክሻችን ጎብጧል። ያዘልንበት ጀርባችን ተመልጧል። በግድ አምጡ እየተባልን የሰጠነው ጥሪታችን ተሟጧል። ከእንግዲህ ግን በቃን ነው ያሉት።

ከልጆቻችን እየነጠቁ በልተውብናል፣ ቀንጃ በሬያችንን እየነዱ አርደውብናል። ኧረ ተው ልጆቻችን እናሳድግ ባልን ጊዜ ተደብድበናል፤ተገርፈናል፤ ታስረናል፤ የምንጮህበት አጥተን፣ መላው ጠፍቶን በጨለማ ውስጥ ኖረናል ይላሉ።

እንዳናርስ በሬዎቻችን ያርዱብናል፣ ማዳበሪያ እንዳናመጣ ያግዱናል። ያለችውን እንዳንበላ ከእጃችን እየነጠቁ ይበሉብናል። ከልጆቻችን ላይ እየመነጨቁ ይወስዱብናል። እንዳንነግድ ወረታችን ያሳጡናል። ልጆቻችን አስተምረን ለወግ ለማዕረግ እንዳናበቃ ትምህርት ቤት ዘግተው ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ ያርቁብናል፤ አቤቱ የፍትሕ ያለህ እያልን ባጅተናል ነው የሚሉት።

ከእኛ በላይ ያስመረሩት፣ ከእኛም በላይ ያወቃቸው የለም። ምንም አይጠቅሙም። ከብራችንን፣ ሃብታችንን፣ ተስፋችንን ሁሉንም ነጥቀው ደሃ አድርገውናል እንጂ ይላሉ።

እንኳን መንግሥት አይዟችሁ አለን፣ ቦታችን ድረስ መጥቶ አወያየን እንጂ ከዚህ በኋላ እያባበሉ መባጀት አያስፈልግም እንታገላቸዋለን ነው ያሉት። እሺ ያሉትን እንመክራቸዋለን። እንቢ ያሉትን ግን አሳልፈን እንሰጣለን። ከዚህ በኋላ በሸለቆ ሌቦች እተተማረሩ መኖር አብቅቷል ይላሉ። ሰው ተወልዶ ባደገበት፣ አግብቶ ወግ ማዕረግ ባየበት መንደር ለምን ይሰቃያል? ዓላማቸው ምንድን ነው? አልገባን ብሏል ነው የሚሉት።

እኛ የምናሳዝናቸው ወገኖች ካሉ በአሻገር ኾነው አይዞህ እያሉ መከራችን ከሚያጸኑት ይልቅ እየመከሩ ይመልሷቸው። ሕዝብ መሮታል ለሰላም ግቡ እያሉ ይንገሩልን። ያ ካልኾነ ግን በተመቻቸ ሀገር ኾነው በለው፣ ግፋ በለው እያሉ መከራችን አያጽኑብን ይላሉ።

አሁን ሰላምን ያሉ ወገኖች ተነስተዋል። ሰላምን ያሉ ድምጾች ተሰምተዋል። ሰላምን ያሉ እጆች ተዘርገተዋል። ሕዝብ አፍሯል። አምርሯል። ምሬቱን በሰላም ገልጿል። ብልሕ ካለ ሰላሙን ይከተለው። ጩኸቱን ይስማው። ያን ጊዜ ሀገሩ ሁሉ ሰላም ይኾናል። ወጥቶ መግባት፣ ደርሶ መምጣት ይኖራል።

ከራሱ በላይ ለሕዝብ የሚያስብ ካለ ጩኸቱን ሰምቶ ሰላምን ይምረጣት። የሰላምን መንገድ ይከተላት። ያን ጊዜ ሕጻናት በደስታ ይቦርቃሉ። ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ። ዘመናቸው የባከነው ሚሊዮን ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ይጓዛሉ። እናቶች ይስቃሉ። አበው በደስታ ይመርቃሉ። የተነፋፈቁት ይገናኛሉ። ውንብድና የበዛባቸው ጎዳናዎች ሰላማዊ ይኾናሉ።

እነኾ ሰላምን ፈልጓት፣ ተከተሏት። አጥብቃችሁም ያዟት። በጥንቃቄም ጠብቋት። እርሷ ከሁሉም ትቀድማለች። ከሁሉም ትልቃለችና።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየህፃናት መብት እና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ።
Next articleይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ ነው!