
ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ የህፃናት ቀን ” የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን በማነፅ ህፃናት ተኮር ተግባራትን እናከናውን “በሚል መሪ ቃል በጎንደር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የአማራ ክልል ሴቶችና ህፃናት ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ብርቱካን ሲሳይ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውሰጥ ያሉ የህፃናት ቁጥር ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የጉልበት ብዝበዛ ፣ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ፣ለተለያዩ ልማዳዊ ድርጊቶች ሰለባ የሆኑ እንዲሁም በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የትምህርት አገልግሎት የማያገኙ ህፃናት ቁጥር ቀላል አለመሆኑን ገልጸዋል።
በህፃናት ላይ የሚደርሱ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ስልቶችን በመቅረጽ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በህፃናት ላይ የሚደርሰውን ማኅበራዊ፣ ስነልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመፍታት እና የህፃናት ጥቅምና መብት ሊያስከበር በሚችልበት ሁኔታ እጅ ለእጅ ተያይዘን በርብርብ ልንሠራ ይገባል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የነገ ሀገር ተረካቢ ህፃናት መብታቸው ተጠብቆ እንዲያድጉ ኃላፊነታችን በአግባቡ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ወራት የህፃናት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ሥራዎች የተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል። ህፃናት የአካባቢያችን ልማት እንዲያውቁ ፣የህፃናት የፈጠራ ሥራዎችን በኢግዚብሽን እንዲያቀርቡ ፣ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ህጻናት የሚማሩት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እና ሌሎች ተግባራዊ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ቀደምት አባቶች ለህፃናት ትኩረት በመሰጠት በእውቀትና በክህሎት የዳበር ዜጋ ለመፈጠር የሚደነቅ ሥራ ይሠሩ እንደነበር አንስተዋል።
ህፃናት ተተኪ ሀገር ተረካቢ በመሆናቸው የሚገባቸውን ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ ይገባል ያሉት ወይዘሮ ደብሬ በህፃናት ላይ ጉዳት በሚያደርሱ አካላት ላይ የህግ የበላይነት እንዲከበር መሰራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶችና ህፃናት ማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ሙሉቀን ብርሃኑ ደግሞ ትምህርት ያቋረጡ ህፃናት ወደ ትምህርት ገበታቸው የመመለስ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በጋራ እንከላከል ሲሉም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
