
ደብረ ታቦር: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በእስቴ ወረዳ እና በመካነ ኢየሱስ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እያስከበሩ ከሚገኙ የጸጥታ ኀይሎች ጋር ተወያይተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የጸጥታ ኀይሎች የሕግ ማስከበር ሥራውን በሚገባ እየፈጸሙ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። “የጽንፈኛው ኀይል ከእኛ ጋር የመዋጋት አቅም የለውም” ነው ያሉት።
ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ ግዳጃቸውን በብቃት እየተወጡ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል። ለተቸገረው ሕዝብ በተሟላ ሁኔታ ለመድረስ እየሠሩ እንደኾነ የተናገሩት የጸጥታ አባላት የጽንፈኛውን ኀይል ጊዜ ሳይሰጡ በማጽዳት የተቀላጠፈ የሕግ ማስከበር ሥራ እየሠሩ ስለመኾኑ ጠቁመዋል።
የአድማ መከላከል፣ የሰላም አስከባሪ እና የሚሊሻ ኀይሉ በጀግንነት ግዳጁን እየፈጸመ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ሕዝቡ ከጽንፈኛው ኀይል እየተነጠለ ለእነርሱ አቅም እየኾናቸው መኾኑንም ተናግረዋል። በየአካባቢው የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ሥራ በመሥራት በአጭር ጊዜ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባልም ነው ያሉት። የወረዳው ሰላም በተሻለ ደረጃ ላይ መኾኑንም ተናግረዋል። ጽንፈኛው ኀይል አሁን ያለው አቅም ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ብቻ ነው ብለዋል።
ጽንፈኛው ኀይል ሰላማዊ አማራጮችን እስካልተቀበለ ድረስ የሕግ ማስከበር ሥራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ጌትነት በዛ እያደረጋችሁት ላለው የጀግንነት ሥራ ክብራ እና ምሥጋና ይገባችኋል ብለዋል። በሠሩት የጀግንነት ሥራ የአካባቢው ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
ከዚህ የበለጠ ኀይል እያሠባሠባችሁ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባችኋል ነው ያሉት። የጸጥታ ኀይሎች የሚጠይቁት ጥያቄ እንደሚመለስም ተናግረዋል። ወረዳዎችን በማቀናጀት የሕግ ማስከበር ሥራውን እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ ለክልሉ ሰላም ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ክብር ይገባችኋል ነው ያሉት። እናንተ ጀግኖች ናችሁ ያሉት ኀላፊው ሕዝባዊ መሠረት ያለው እና ቁርጠኝነት ያለው ኀይል ሁልጊዜም አሸናፊ ነው ብለዋል።
ጽንፈኛው ኀይል ለአማራ ሕዝብ የማይጠቅም የዘራፊ ሥብሥብ መኾኑን ነው የተናገሩት። ጀግኖች እና ጽናት ያላችሁ መኾናችሁን እኛ ሳንኾን ሕዝብ መስክሮላችኋል ብለዋል። በሥነ ምግባር የታነጸ ሠራዊት ምንጊዜም አሸናፊ መኾኑን አንስተዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ለጸጥታ ኀይሎች መደረግ ያለበትን ሁሉ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ለጸጥታ ኀይሎች ልዩ ትኩረት እንደሚሠጥም ተናግረዋል። ራሳቸውን ከየትኛውም የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ነጻ በማድረግ ለሕዝብ ሰላም እንዲሠሩም ጠይቀዋል። ሠርጎ ገቦች እንዳይኖሩ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
ጽንፈኛው ኀይል በሰላም እጁን እንዲሰጥ ማድረግ ይገባል ያሉት ኀላፊው የሰላም አማራጭን በሚገፋው ኀይል ላይ ግን የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ የጸጥታ ኀይሉ አስደናቂ የግዳጅ አፈጻጸም እየተወጣ መኾኑን ገልጸዋል። በየአካባቢው የሚንቀሳቀሰውን ጽንፈኛ ቡድን እያሳደደ ሰላም እያስከበረ ነውም ብለዋል።
የክልሉ የጸጥታ ኀይል የማድረግ አቅሙ ከፍ እያለ እና ጽንፈኛውን እያሽመደመደ መኾኑን ነው የተናገሩት። ጽንፈኛው ቡድን እየተሽመደመደ እና እየፈራረሰ መኾኑን ገልጸዋል። የተሽመደመደውን የጽንፈኛ ኀይል በሕግ ማስከበር አደብ ማስገዛት እና ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
ሕዝቡ ለጸጥታ ኀይሉ ትልቅ አቅም እየኾነ መምጣቱን ነው የተናገሩት። በየመንገዱ የሚገኘውን ዘራፊ ቡድን ማጥፋት እንደሚገባም ገልጸዋል።
በቀጣይም የሕግ ማስከበር ሥራውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። የጀመሩትን የጀግንነት ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን