
ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳድር ትምህርት መምሪያ መጭውን የተማሪዎች ክልላዊ ፈተና አስመልክቶ ለየትምህርት ቤቶች ርእሳነ መምህራን፣ ለመምህራን ማኀበር ተወካዮች፣ ለሱፐርቫይዘሮች እና ከልዩ ልዩ መሥሪያ ቤቶች ለተወከሉ የሥራ ኀላፊዎች ገለጻ እና ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የጠይማ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የጉድኝት ሱፐርቫይዘር ታደለ ቢሻው 570 የስድስተኛ እና 581 የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ክልላዊ ፈተናውን ይወስዳሉ ብለዋል። ለእነዚህን ተማሪዎች በተለየ ሁኔታ የማጠናከሪያ እና የማካካሻ ትምህርት እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል።
ተማሪዎች ቀኑን ሙሉ የቤተ መጽሐፍት አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ያሉት አቶ ታደለ በቂ የሥነ ልቦናም ዝግጅት በማላበስ እና የራስ መተማመናቸው ከፍ እንዲል ተደርጓል ነው ያሉት።
የአዲስ ዓለም ትምህርት ቤት የጉድኝት ማዕከል ሱፐርቫይዘር እናንየ ይግዛው በጉድኝታቸው ስድስተኛ ክፍል 699 እንዲሁም ስምንተኛ ክፍል 791 ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ ብለዋል።
የባከነ የትምህርት ክፍለ ጊዜ እንዲካካስ ተደርጓል ነው ያሉት ሱፐርቫይዘሯ። በዚህ ዓመት ጥሩ ውጤት ይመዘገባል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ተናግረዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የፈተና ዝግጅት እና አሥተዳደር ባለሙያ አበበ አያሌው የስድስተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ፈተና በሁለት ዙር እንደሚሰጥ ተናግረዋል። የመጀመሪያው ዙር ፈተና በሰኔ ወር መጀመሪያ የሚሰጥ ሲኾን ሁለተኛው ዙር በመስከረም 2018 ዓ.ም ይሰጣል ነው ያሉት።
የትምህርት መምሪያ ኀላፊው ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) የትምህርት ሥራ ማጠቃለያው ፈተና መኾኑን አስታውሰው፤ የትምህርት ባለ ድርሻዎች ደግሞ በሥራቸው የሚገመገሙበት ነው ብለዋል።
እንደ ከተማ አሥተዳደር ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘገቡ ተሠርቷል ያሉት ዶክተር ሙሉዓለም ከባሕር ዳር እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ድገፍ ተደርጓልም ነው ያሉት።
ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ትምህርት በመስጠት የትምህርት ይዘቶች እንዲሸፈኑ መደረጋቸውን ነው ዶክተር ሙሉዓለም ያብራሩት።
ተማሪዎች ኩረጃን ተጠይፈው በራሳቸው እንዲተማመኑ የማድረግ ሥራ ግን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅ መምሪያ ኀላፊው አሳስበዋል።
መምህራን ቦንብ እየፈነዳባቸው፣ “ችግሮችን ተጋፍጠው ሙሉ ቀን አስተምረዋል፤ ያሉት ዶክተር ሙሉዓለም የልፋታቸው ውጤት የሰመረ እንዲኾን ፈተናው በሥርዓት መሰጠት አለበት” ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም በእኔነት ስሜት መሥራት እንዳለበት ነው ያብራሩት።
ወላጆች ከትምህርት ቤቶች ጋር ተቀራርበው መሥራታቸውን ያወደሱት ዶክተር ሙሉዓለም በዚህ አዎንታዊ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል። ጅምሩም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የገለጹት።
በ2017 የትምህርት ዘመን 66 የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች ስድስተኛ ክፍል ላይ 7 ሺህ 514 ተማሪዎች እንደሚያስፈትኑም መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል። በ55 ትምህርት ቤቶች ደግሞ የስምንተኛ ክፍል ፈተናን 7 ሺህ 752 ተማሪዎች እንደሚወስዱም ገልጸዋል።
ፈተናው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ትምህርት ቤቶች የግቢ ደህንነትን ለማስጠበቅ ከፓሊስ ጣቢያዎች ጋር ተናበው መሥራትም ይገባቸዋል ብለዋል።
በየክፍል ደረጃዎች የሚሰጠው ፈተናም በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል ትብብር እንዲያደርግ ዶክተር ሙሉዓለም ጥሪ አቅርበዋል።
የ2017 የትምህርት ዘመን የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከሰኔ 3 እስከ ሰኔ 4 /2017 ዓ.ም ይሰጣል። የስድስተኛ ክፍል ፈተና ደግሞ ከሰኔ 5 እስከ ሰኔ 6 /2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ዘጋቢ: ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን