የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ስለ ሀገር ሰላም ዱአ በማድረግ ታስቦ የሚውል ታላቅ በዓል ነው።

3

ሰቆጣ: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 446ኛው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሰቆጣ ከተማ በታላቁ አንዋር መስጅድ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ተከብሯል።

በበዓሉ መልዕክት ያስተላለፉት የአንዋር መስጅድ ኢማም ሼህ ሐጅ መሐመድ አደም በዓሉ ለአላህ ምስጋና የሚቀርብበት እና “ስለ ሀገር ሰላም ዱአ የሚደረግበት ታላቅ በዓል መኾኑን” ተናግረዋል።

የሰቆጣ ከተማ ሕዝበ ክርስቲያን እና ሕዝበ ሙስሊሙ በመፈቃቀር እና በመቻቻል እንደኖረ ሁሉ ዛሬም በፍቅር በዓሉን ማክበራቸው እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል።

በአንዋር መስጅድ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳደሪ ኃይሉ ግርማይ እንደ ሀገር ከገባንበት የሰላም እጦት እንድንወጣ ወጣቱ ለሰላም ዘብ በመቆም አለበት ብለዋል።

ሼኾች ስለ ሀገር ሰላም በመጸለይ እና የሀገር ሽማግሌዎች ደግሞ ወጣቱን በመምከር በዓሉን ማክበር ይገባል ነው ያሉት።

በዋግ ላለው የሰላም መጽናት የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ያወሱት አቶ ኃይሉ ይህንን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

የዒድ አል አድሃ በዓል የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት እና ደጋፊ ያጡ አዛውንቶችን በመጎብኘት የሚከበር በዓል መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ ናቸው።

ይህንን መልካም እሴት የበዓላት ቀኖችን ብቻ ጠብቀን የምናከብራቸው ሳይኾኑ ዘወትር ሊተገበሩ የሚገባቸው መልካም ተግባራት መኾናቸውንም ከንቲባው ጠቁመዋል።

በዓሉን ለማክበር በአንዋር መስጅድ ያገኘናቸው ሐጅ አብድራህማን ከማል እና ወጣት ከማል መሐመድ በዓሉን በአንድነት እና በፍቅር በማክበራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የሀገርን ሰላም ለማጽናትም ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመሥራት ሰላሟ የተጠበቀች ሀገርን ለመገንባት እንደሚሠሩ አስተያየት ሰጭዎቹ ነግረውናል።

1ሺህ 446ኛው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ሲከናወን የዋለ ሲኾን በበዓሉም የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር መሪዎች፣ ሼኾች፣ ኢማሞች፣ የሃይማኖቱ ተከታዮች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

ዘጋቢ: ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article
Next articleችግሮችን ተጋፍጠው ያስተማሩ መምህራን የልፋታቸው ውጤት እንዲሳካ ፈተናው በሥርዓት መሰጠት አለበት።