
“በአንድነት ስትነሱ ሰላማችሁን አረጋግጣችሁ ታሪክ ትሠራላችሁ” አቶ ይርጋ ሲሳይ
ደብረ ታቦር: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከመካነ ኢየሱስ ከተማ አሥተዳደር እና ከእስቴ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት እሱባለው መሰለ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በመከራ እና በችግር ውስጥ ቆይተናል ብለዋል። ልጆቻችን ሳይማሩ ቀርተዋል፣ ከዚህ በላይ መከራ በቃን ነው ያሉት። ችግሩ በውይይት እና በስምምነት እንዲፈታም ጠይቀዋል።
ከዚህ በላይ ልጆቻችን ከትምህርት ቤት ርቀው እንዲኖሩ አንፈቅድም ብለዋል። በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የመጀመሪያ ተጎጅው ሕዝብ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ሕዝብ ከልማት እና ከንብረቱ ሳይኾን መክረሙንም ተናግረዋል።
የሰላም አማራጭ የተቀበሉትን እናመስግናለን፣ ሌሎችም እንዲገቡ እንጠይቃለን ነው ያሉት። በጫካ የሚገኙ ኃይሎች ዓላማቸው ገንዘብ መሰብሰብ ነው ሌላ ዓላማ የላቸውም፣ ዓላማ የሌላቸው ሌቦች ሕዝብን እያሰቃዩ ነው፣ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ እናስመልሳለን በሚል ሰበብ ሕዝብ በሌሎች ኢትዮጵያውያን በጥርጣሬ እንዲታይ አድርገዋል ነው ያሉት።
ታላቁን እና የተከበረውን የአማራ ክልል ሕዝብ አንገት የሚያስደፋ ተግባር መፈጸማቸውንም ተናግረዋል።
ለሀገር ሰላም እና ለሉዓላዊነት መስዋዕትነት የሚከፍለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሌቦች ሲጠቃ ዝም ብለን ማየት የለንም ነው ያሉት። ከእኛ በላይ የሚኾን ጽንፈኛ ኃይል የለም በአንድነት መታገል አለብንም ብለዋል።
የማዳበሪያ አቅርቦት በሥፋት እንዲቀርብላቸው እና ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የእስቴ ሕዝብ ላደረገልን አቀባበል ምስጋና አለን ነው ያሉት። የአማራ ክልል መንግሥት በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ የጸጥታ ኃይል እና በሕዝቡ የተጀመረውን ሰላም የማስቀጠል ጽኑ አቋም አለው ብለዋል።
የመጀመሪያውም የመጨረሻውም አማራጫችን ሰላም ነው ያሉት ኀላፊው በጫካ የገቡ ኃይሎችን መክራችሁ እንድታስገቡ የመንግሥት ጥሪ ነው ብለዋል። በጫካ የሚገኙ ኃይሎችን በሰላም ካስገቡ አካባቢዎች ትምህርት እንዲወስውዱም አሳስበዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ጽንፈኛ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት። መንግሥት እና ሕዝብ የበደሉትን ይቅር እንደሚሉም ተናግረዋል።
ጽንፈኞች ትምህርት እያቋረጡብን፣ መምህራንን እየገደሉብን፣ ንጹሐንን እያገቱብን፣ ማደበሪያ በወቅቱ እንዳይገባ እያደረጉብን ነው ብለዋል። መንግሥት ይቅርታ ስለሚያደርግ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሸማግሌች እንድታስገቡ እንጠይቃለን ነው ያሉት። ከሰላም አማራጭ ጎን ለጎን ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
“አንድ ስትኾኑ በማንም ጠላት አትሸነፉም፣ ድል ታደርጋላችሁ፣ በአንድነት ስትነሱ ሰላማችሁን አረጋግጣችሁ ታሪክ ትሠራላችሁ” ብለዋል። መከራውን እና ግፉን በቃ ብላችሁ ተነሱ ነው ያሉት።
ችግሩን ዝም ብለን የምንመለከተው ከኾነ የባሰ መከራ ይመጣል፣ በአንድነት፣ በጋራ መስዋዕትነት ሰላማችን ማስከበር አለብን ብለዋል። አሁን ያለው ሰላም የመጣው በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች መስዋዕትነት መኾኑን አንስተዋል።
የጸጥታ ኃይሎችን እንዲያግዙም አሳስበዋል። አማራ ታላቅ ሕዝብ ነው ያሉት ኀላፊው በመስዋዕትነቱ ያመጣውን ድል ለመንጠቅ የሚዞር ኃይል አለ ንቁበት፣ አንድነታችሁን አጠናክሩ፣ ለሕዝብ ጥያቄ አስመልሳለሁ የሚለው ጽንፈኛ ውሸቱን ነው፣ ይልቁንስ የአማራ ሕዝብ በመስዋዕትነቱ ያመጣቸውን ድሎች አሳልፎ ለመስጠት ከጠላቶች ጋር እየሠራ ነው ብለዋል።
አማራጩ አንድነት እና አብሮነት ነው ያሉት ኀላፊው በመከፋፈል እና በመለያየት የውጭ እና የውስጥ ጠላቶችን ማሸነፍ እንደማይችል ተናግረዋል። ወጣቶች ሰላምን ለማስከበር እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የጀመሩትን የሰላም ማስከበር ሥራ አጠናክረው በመቀጠል የአካባቢውን ሰላም እንዲያረጋግጡም አሳስበዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል መስዋዕትነት እየከፈለ ማዳበሪያ እያመጣ ነው ያሉት ኀላፊው አርሶ አደሮች ለእነርሱ ሲሉ መስዋዕትነት የሚከፍለውን የጸጥታ ኃይል ማገዝ አለባችሁ ብለዋል። በየመንገዱ ማዳበሪያ የሚያስቆመውን፣ የሚዘርፈውን እና ሹፌር የሚያግተውን መታገል እንደሚገባም አሳስበዋል።
መንግሥት በትኩረት ማዳበሪያ ለማድረስ እንደሚሠራም ተናግረዋል። ሰላም ካለ ለእስቴ እና ለመካነ ኢየሱስ የሚከለከል የልማት ሥራ እንደሌለም ተናግረዋል። በችግር ውስጥም ተኾኖ ከሀሙሲት- እስቴ- ስማዳ ያለውን መንገድ እያስቀጠሉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
ልማት በስፋት እንዲመጣ ጽንፈኛውን ማውገዝ እና መታገል እንደሚገባቸው ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት ለአካባቢው ልማት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። ልማቱ እንዲፋጠን ግን ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን