
ደብረታቦር: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በነፋስ መውጫ ከተማ አሥተዳደር የሲራክ ጫኔ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን እና መምህራንን ፈትኖ ይቀበላል። ወደዚህ ትምህርት ቤት የሚገቡ ተማሪዎች እና መምህራን በብቃታቸው የተመሰከረላቸው እና የተዘጋጀውን ፈተና ያለፉ ብቻ ናቸው።
በስምንተኛ ክፍል ጥሩ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ለፈተና ይቀርባሉ። ፈተናውን ያለፉ ወደ ልዩው ትምህርት ቤት ይቀላቀላሉ። ልዩ ትምህርት ቤቱ በ2017 ዓ.ም ጀምሮ በፈተና ብቁ የኾኑ ተማሪዎችን ተቀብሎ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎችን ማስተማር ጀምሯል።
የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችም በተመረጡ መምህራን የተሻለ ትምህርት እየተማርን ነው፣ ነገ ሕልማችንን መኖር እንድንችል መምህራን በትጋት እያስተማሩን ነው ብለዋል።
ተማሪ ኾነልኝ ደፋሩ ትምህርት ቤቱ የተመረጡ ተማሪዎችን አወዳድሮ በመፈተን የተመረጡ ተማሪዎችን እንደሚያስተምር ገልጿል። ለዚህም ልዩ ትምህርት ቤት ተብሏል ነው ያለው።
ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎች የተለያዩ እገዛዎችን እንደሚያደርግ የተናገረው ተማሪ ኾነልኝ ለተማሪዎች ቁርስ እና ምሳ ምግብ እንደሚያቀርብ አስታውቋል። ከሌሎች ትምህርት ቤቶች በተለዬ መልኩ ትምህርት የሚሰጥበት የሰዓት ርዝማኔ ሰፊ ነውም ብሏል።
መምህራን ከመደበኛ ክፍለ ጊዜ ባለፈ በሌሎች ጊዜያትም ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸውም ገልጿል። ተወዳዳሪ ተማሪ ለመኾን በርትተው እያጠኑ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ልዩ ትምህርት ቤቱ አዲስ በመኾኑ ቤተ ሙከራ እንዳልተሟላለት ገልጿል። በትምህርት ቤቱ ገና የመብራት አገልግሎት እንዳልተዘረጋለትም አንስቷል። የጎደሉት እንዲሟሉም ጠይቋል። መምህራን ከእኛ ላይ ታላቅ ተስፋ ጥለው በትጋት እያስተማሩን ነውም ብሏል።
ተማሪ ማሕደር ምትኩ ብቁ የኾኑ ተማሪዎች እና መምህራን ፈተና አልፈው የሚገናኙበት ትምህርት ቤት በመኾኑ ልዩ ነው ብላለች። ከሌሎች ትምህርት ቤቶች በተለየ መልኩ የትምህርት አሰጣጡ ሰፊ እና ጠንካራ መኾኑንም ገልጻለች።
ሁሉም ተማሪዎች ጎበዞች እና ረጅም ጊዜያቸውን ለጥናት ስለሚያውሉ ውድድር ውስጥ እንድንገባ እና የተሻልን እንድንኾን አድርጎናል ነው ያለችው።
መምህራን ነጋችን አስበው ያግዙናልም ብላለች። ተማሪ ማሕደር በብርታት ተምራ ዶክተር የመኾን ሕልም እንዳላትም ነግራናለች።
የሲራክ ጫኔ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ክንድዬ ተስፋው ትምህርት ቤቱ በ2017 ዓ.ም ጀምሮ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተብሎ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል። በስምንተኛ ክፍል ውጤታቸው ተመልምለው፣ የመግቢያ ፈተና ወስደው ያለፉ ተማሪዎች ብቻ የሚገቡበት መኾኑንም ገልጸዋል።
መምህራንም ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው እና የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀውን ፈተና አልፈው የገቡ ናቸው ብለዋል። የትምህርት ቤቱ መሪዎችም በፈተና የገቡ መኾናቸውን ተናግረዋል። ትምህርት ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ 52 ተማሪዎችን መቀበሉን የተናገሩት ርእሰ መምህሩ ሁለት ተማሪዎች በቤተሰብ ችግር ምክንያት ወደ ሌላ ቦታ ሲሄዱ 50 ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው ብለዋል።
በትምህርት ቤቱ ሰፊ የትምህርት ጊዜ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ተማሪዎች እስከ 10 ሰዓት ድረስ በትምህርት ቤት እንደሚውሉም አንስተዋል። ትምህርት ቤቱ ለሀገር የሚጠቅሙ ተማሪዎችን እንደሚያወጣ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት መኾኑንም ገልጸዋል። በትምህርት ቤቱ ነገ ሀገር የምትኮራባቸው እና ተስፋ የምታደርጋቸው በሥነ ምግባር፣ በዕውቀት እና በአመለካከት ጥሩ የኾኑ ተማሪዎች አሉ ነው ያሉት።
መምህራን የተማሪዎቹን ህልም እውን ለማድረግ በትኩረት እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። የመብራት እና የቤተ ሙከራ አገልግሎት እንዲሟላም ጠይቀዋል።እንዲህ አይነት ትምህርት ቤቶች እንዲሠፉ መንግሥት እና ማኅበረሰቡ በትብብር መሥራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
የነፋስ መውጫ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደጀን አከለ ለትምህርት ከተማ አሥተዳደሩ፣ የላይ ጋይንት ወረዳ እና ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል። በትምህርት ቤቶች የተጓደሉ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ እየሠራን ነው ብለዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብም ለትምህርት ቤቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸውልናል ነው ያሉት። ባለሀብቶችም ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። በቀጣይ በርካታ ተማሪዎችን እንዲቀበል እና ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲወጣበት በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል።
ልዩ ትምህርት ቤቱ ገና ጀማሪ በመኾኑ ብዙ ጉድለቶች አሉበት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የመብራት ችግሩን እና ሌሎች ችግሮችን በመፍታት የተሻለ ትምህርት ቤት እንዲኾን እየሠራን ነው ብለዋል። የጎደለውን በመሙላት የተሻለውን ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት።
የአካባቢው ማኅብረሰብ የተሻለ መማር ማስተማር እንዲኖር ሰላሙን በመጠበቅ፣ ከሌሎች አካባቢዎች ወደ ልዩ ትምህርት ቤቱ የሚመጡ ተማሪዎችን በመንከባከብ፣ የጎደለውን በመሙላት የራሱን ደርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል። ትምህርት ቤቱ ብቁ ተማሪዎችን ለመቅረጽ ተስፋ ያለው መኾኑንም ተናግረዋል።
በትምህርት ቤቱ ከመማር ማስተማር ባለፈ የግብርና ሥራዎች እንዲሠሩበት ታሳቢ ኾኖ የተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። የታሰበው እንዲሳካም ጥረታችን እንቀጥላለን ብለዋል።
የላይ ጋይንት ወረዳ አሥተዳዳሪ ግርማ ይስማው ትምህርት ቤቱ ልሕቀት ያላቸው ተማሪዎች የሚፈጠሩበት፣ የአጎራባች ወረዳ ተማሪዎችን ተሳታፊ ያደረገ መኾኑን ነው የተናገሩት። ልሕቀትን ማዕከል አድርጎ ንድፈ ሀሳብን ከተግባር ጋር አዛምዶ ለሀገር ጠቃሚ የኾኑ ተማሪዎችን የሚያፈራ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ ጀማሪ በመኾኑ ጉድለቶች አሉት ያሉት አሥተዳዳሪው ጉድለቶችን በመሙላት ትምህርት ቤቱ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። ማኅበረሰቡም ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
የላይ ጋይንት ወረዳ ትምህርት ቤት እንዲከፈት ካደረገው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ ትምህርት ቤቱ ሥራውን እንዲያስሄድ እያደረገ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ የተሟላ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲኾን ፍላጎት እንዳላቸውም አንስተዋል። ለሀገር የሚጠቅሙ ተማሪዎችን ለማፍራት ሁሉም ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባውም አመላክተዋል።
ትምህርት ቤቱ ወደፊት የልሕቀት ማዕከል እንደሚኾንም ዕምነት አለን ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን