
ጎንደር: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ 1 ሺህ 446ኛው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ተከብሯል።
በዓሉ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በተገኙበት በአጼ ፋሲል ስታዲዬም ነው የተከበረው።
በበዓሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሐጅ አንዋር ቃሲም የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የመስዋዕት በዓል ነው ብለዋል። ሕዝበ ሙስሊሙ ይህን ለማስታወስ በዒድ ቀን እርድ እንዲያከናውኑ ታዘዋል ነው ያሉት።
“እስልምና ሃይማኖት ለሁሉም ሰላም መኾንን በአስተምህሮቱ ይገልጻል” ያሉን ደግሞ የጎንደር ከተማ ኡለማ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ምስጦፋ ሞላ ናቸው። በዓሉን ስናከብርም በሰላም፣ በፍቅር እና የተቸገሩትን በማሰብ ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዒድ አል አድሃ በፈጣሪ እና በሰው ልጅ መካከል ያለውን ጽኑ ፍቅር እና መታዘዝ የተገለጠበት እንደኾነ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ተናግረዋል።
ዒድ አል አድሃ የእርድ በዓል ነው ያሉት ወይዘሮ ደብሬ በዓሉን ስናከብር እንሰሳትን በማረድ እና ሲሶውን ለአቅመ ደካሞች በመስጠት ሊኾን ይገባል ብለዋል።
በዚህ ዘመን በብዙ ምክንያቶች የተቸገሩ ወገኖች በየሰፈሩ ያሉ በመኾኑ ያለንን በማካፈል የአላህን ትዕዛዝ መፈጸም እንደሚገባም አንስተዋል። በተለያየ አጋጣሚ እየተከሰተ ያለውን የሰላም እጦት በጋራ መከላከል እንደሚገባም መልዕልት አስተላልፈዋል።
የሃይማኖቱ ተከታዮች በበኩላቸው ደጋፊ የሌላቸውን ወገኖች በማገዝ እና በማስታዎስ በዓሉን እያከበሩት መኾኑን ነግረውናል።
ዘጋቢ: አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን