
ደባርቅ: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለ1 ሺህ 446ኛ ጊዜ የሚከበረው የዒድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች እየተከበረ ነው።
የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ታላቅ ከሚባሉ ኢስላማዊ የሃይማኖት በዓላት መካከል አንዱ ነው።
በዓሉ በዳዕዋ፣ በሰላት፣ በዝየራ እና በሌሎች ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚከበር ሲኾን የአብሮነት እና የመተሳሰብ ቀን እንደኾነም ይነሳል።
የሰሜን ጎንደር ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ከድር ዳውድ እንደገለጹት የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል የመስዋዕት እና የዕርድ በዓል ነው።
ስለኾነም ሕዝበ ሙስሊሙ የተለመደ ሃይማኖታዊ እና ሀገራዊ የመተሳሰብ እና የመረዳዳት ዕሴቱን በማጉላት በዓሉን በጋራ ሊያከብር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በደባርቅ ከተማ ከስምንት በላይ ሰንጋ፣ ከ70 በላይ በግ እና ፍየል ታርዶ አቅም የሌላቸውን ተደራሽ የማድረግ እና የማሰብ ሥራ መሠራቱም ተገልጿል።
የዞኑ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አህመድ የሱፍ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚገኙ የሃይማኖቱ ተከታዮች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ አቅመ ደካሞችን የመደገፍ ሥራ ማከናዎናቸውን ተናግረዋል።
ይሄም በጎ ተግባር በሃይማኖታዊ አስተምህሮው መሠረት በፈጣሪ ዘንድ ትልቅ ዋጋ የሚያሰጥ ነው ብለዋል። የድጋፍ መርሐ ግብሩ ከዚህ በፊትም የነበረ እና አሁንም በተጠናከረ እና በተደራጀ መንገድ ሊቀጥል የሚገባው አርዓያነት ያለው ተግባር መኾኑንም ገልጸዋል።
የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ መምህር ከድር ሙላቴ በዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቶቹ በተጨማሪ ዘመድ፣ ጎረቤት፣ ጓደኞች እርስ በእርስ የሚጠያየቁበት የዝየራ እና የዳዕዋ ቀን መኾኑንም ተናግረዋል።
በዚህ ቀን አስታዋሽ እና ደጋፊ ያጡ አቅመ ደካሞችን በገንዘብ እና ቁሳቁስ ከመደገፍ በተጨማሪ በሥነ-ልቦና የማንቃት እና የመጎብኘት ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በዓሉ በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም መከበሩም ተመላክቷል።
በበዓሉ መልዕክት ያስተላለፉት የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ልዑል መስፍን ሕዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ሰላም እና ሁለንተናዊ ዕድገት በንቃት ሲሳተፍ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በቀጣይም ሕዝበ ሙስሊሙ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ሕግ እና ደንብን መሠረት አድርገው ለቀረቡ የተለያዩ ጥያቄዎች አፋጣኝ መልስ ለመስጠት እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን