መስዋዕትነት በእምነት ድል የኾነበት ቦታ – የአረፋ ተራራ

70

ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ኢድ አል አድሃ (አረፋ ) ተናፋቂ በዓል ነው። በየዓመቱ በጉጉት ይጠበቃል፤ በፍቅር በአንድነት፣ በድምቀት ይከበራል።

ዒድ አል አድሃ የእዝነት እና የአብሮነት በዓል ነው። በዚህ ታላቅ በዓል ፍፁም መተሳሰብ ይንፀባረቃል፣ ፍቅር ጎልቶ ይወጣል፣ ርህራሄ በተግባር ይገለጣል። የፈጣሪ ሥራ እየታወሰ አብሮነት በእምነት ታጅቦ ያለው ለሌለው ያካፍላል፣ ባዳ እና ዘመድ ሳይለይ በኅብረት ይከበራል።

በእስልምና ሃይኖት ተከታዮች ዘንድ እንደ ቅዱስ ሥፍራ የምትታየው የሳዑዲዋ መካ ደግሞ በዓሉ በድምቀት ይከበርባታል። በመላው ዓለም የሚገኙ የሃይማኖቱ ተከታዮች በዓሉን ለመታደም ወደ መካ ያመራሉ፡፡ በዚህ ቦታ ደርሰው መታደም ደግሞ መባረክ ነው።

በሳዑዲ አረብያ ከመካ ከተማ በደቡባዊ ምስራቅ አቅጣጫ በ20 ኪሎ ሜትር ገደማ አረፋ የሚባል ተራራ ይገኛል። “ጀበል አራፋት” እየተባለም ይጠራል።

እንደ ሃይማኖቱ አስተምህሮ አረፋ ተራራ ወይም “ጀበል አራፋት” “የምኅረት ተራራ” የሚል ትርጓሜ እንዳለው ይነገራል። የአረፋ የጸሎት ቀን በዚህ በተቀደሰ ታላቅ ተራራ ስያሜ የጸና ሃይማኖታዊ በዓል ነው፡፡

የአረፋ ተራራ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የዓለም ኢስላም ሁሉ ድኅነት የተገለጠበት ቅዱስ ሥፍራ ነው ተብሎ ይታመንበታል፡፡

በአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የደዓዋ እና ትምህርት ዘርፍ ኀላፊ ሼሕ ሙሐመድ ኢብራሂም ነብዩ መሐመድ በአረፋ ተራራ ስር አርፈው ውሏቸውን በጸሎት ያሳለፉበት ቅዱስ ቦታ ነው በማለት ይገልጻሉ

ነብዩ መሐመድ በዚች ስፍራ ልዩ ልዩ ተዓምራትን በማከናወን ለሕዝባቸው አሳይተዋል ብለዋል። ነብዩ መሐመድ በአረፋ ተራራ ቋጥኝ ስር ቆመው ጸሎት አድርገው “እኔ ከዚህ ቦታ ቆሜአለሁ፤ አረፋ ሁሏም ሥፍራ መቋሚያ ናት” ብለው ተናግረው በቅዱስ ቁርዓን ያጸኗት መኾኑን ነው የገለጹት።

የተራራውን ስያሜ በተመለከተ ታሪካዊ ዳራው በተለያየ እንድምታ የሚገለጽ እንደኾነ ነው ሼህ ሙሐመድ የገለጹት። ከእነዚህም መካከል አንዱ ሰዎች በቦታው ተገኝተው ሃጢታቸውን አውቀው የሚማጸኑበት፣ የሚናዘዙበት እና ከአሏህ ጋር በጸሎት የሚተዋወቁበት “አረፈ” ከሚለው ቃል የተወሰደ መኾኑን ይገልጻሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ሼህ ሙሐመድ እንደገለጹት አባታችን አደም እና እናታችን ሐዋ ከጀነት ወደ መሬት ውረዱ በተባሉበት ሰዓት በተለያየ ቦታ አርፈዋል። በኋላ ላይ በዚህ ቦታ ተገናኝተው “አወቅኸኝ” “አወቅሽኝ”(አረፍትኪ አረፍትከ) የተባባሉበት በመኾኑ ስያሜው ከዚህ የመጣ እንደኾነ ይገለጻል ነው ያሉት።

እንደ ሼህ ሙሐመድ ገለጻ የሐጂ ተጓዦች ከሚያከናውኗቸው ዐበይት ሃይማኖታዊ ተግባራት መካከልም የአረፋ ተራራን በመውጣት ሃይማኖታዊ ሥነ ስርዓቶችን በሥፍራው መፈጸም ይኖርበታል ብለዋል።

አረፋ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ጽናት እና ተዓምራት የተስተናገዱበት እንደኾነም ተናግረዋል። ዛሬ ላይ ሚሊዮኖች በሳዑዲ አረቢያ አረፋ ተራራ ላይ ተሰባስበው የአረፋ ቀንን እንደሚያከብሩ አመላክተዋል።

አረፋ ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር በጸሎት እየተገናኙ የዓለም ሰላም የሚለመንበት ቅዱስ ተራራ እና ተናፋቂ ቀን ነው፡፡ አረፋ የመዳን እና የጸሎት ቀን በዓል ኾኖ በዓለም ሁሉ ይከበራል፡፡

በሒጅራ ቀን አቆጣጠር 12ኛው ወር 9ኛው ቀን ላይ ሰዎች ተሰባስበው ወደ ተራራው በመውጣት የሚከወን አንዱ የሐጅ ሥርዓት መኾኑን ገልጸዋል።

ከአረፋ ቀን ቀጥሎ በ10ኛው ቀን ደግሞ በየዓመቱ የኢድ በዓል እንደሚከበር ነው የገለጹት። ኢድ አል አድሃ ፈተናን በጽናት፣ ውጣ ውረድን በብርታት፣ መስዋእትነትን በእምነት ድል አድርገው የተሻገሩበት በዓል ነው፡፡

ሌላው በዚህ ዕለት ነብዩ ኢብራሂም አንዱን ልጃቸው ኢስማኤልን በአላህ ትእዛዝ ለመስዋዕት ሲያዘጋጁ በምትኩ ሙክት ከአላህ መቅረቡን የሚያስታውስ በየዓመቱ የሚከበር በዓል መኾኑን ገልጸዋል።

የአሏህ እዝነት እና ታላቅነት፣ የነብዩ ኢብራሂም እምነት እና ጽናት፣ የልጃቸው ኢስማኤል ታዛዥነት እና ቅንነት በታምራት ታጅቦ የተገለጠበት የመዳን በዓል ነው፡፡

በዓለም ላይ ሁሉ በዒድ ዕለት በግ፣ ፍየል፣ ከብት እና ግመል ታርዶ ድሆች ሳይቀር ስጋ የሚቀምሱበት እንደኾነም አብራርተዋል፡፡

ሙስሊሞች የመስዋዕትነት በዓሉን እርድ በመፈጸም፣ በጋራ በመጸለይ እና ከፈጣሪ ምኅረትን የሚያስገኙ በጎ ተግባራትን በማከናወን እንደሚያሳልፉትም አመላክተዋል።

በዚህ ዕለትም በቤቱ ከሚያርደው ዕርድ አንድ ሦስተኛውን ለሌለው ማካፈል ሃይማኖታዊ ግዴታ እንደኾነም ገልጸዋል። ያለውና የሌለው፣ ሃብታም እና ድሀ እኩል በደስታ በዓሉን ያክብራሉ ነው ያሉት።

በዒድ በዓል በቤቱ የሚያርደውን ለሌለው ማካፈል፣ እንግዳ ተቀብሎ ማስተናገድ፣ ወላጅ ያለው ወላጅ ከሌለው በጋራ የሚውልበት በዓል እንደኾነም ገልጸዋል።

ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleይቅርታ የአሸናፊዎች ምርጫ ነው።
Next articleየአረፋ በዓልን ሃይማኖታዊ የመረዳዳት ዕሴቱን በማጉላት ማክበር ይገባል።