
ደብረ ታቦር: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከመካነ ኢየሱስ ከተማ አሥተዳደር እና ከእስቴ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት እሱባለው መሰለ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የእስቴ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ማንተፋርዶ ሞላ የተፈጠረው ችግር ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል። ጽንፈኛው ኃይል በሕዝብ ላይ ሰቆቃ የሚያበዛ መኾኑንም ገልጸዋል። አሁን ላይ ማኅበረሰቡ የችግሩን ብዛት ተመልክቶ ለሰላም መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ በየአካባቢው እየተወያየ ሰላምን ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ የእስቴ ሕዝብ የተከበረ፣ በራሱ ላብ የሚያድር፣ ምግባረ ብልሹዎችን የሚጸየፍ፣ ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ጀግና ሕዝብ ነው ብለዋል።
ባለፉት ጊዜያት ማኅበረሰባችን ለከፋ ችግር ተዳርጎ ቆይቷል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ጽንፈኞች በማኅበረሰባችን ላይ ጭካኔ ሲያሳዩ ቆይተዋል ነው ያሉት። ጽንፈኛው ኃይል ዓላማ የሌለው፣ ንጹሐንን የሚገድል፣ ንብረት የሚዘርፍ ሥብሥብ ነው ብለዋል።
ጽንፈኞች በዞኑ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውንም አንስተዋል። የግል ኪሳቸውን ለማድለብ የሚሠሩ ኃይሎች መኾናቸውንም ገልጸዋል። መንግሥት አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን በርካታ ሥራዎችን መሥራቱንም ተናግረዋል።
በተሠሩ የፖለቲካ እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች በርካታ ታጣቂዎች በሰላማዊ መንገድ መግባታቸውንም ገልጸዋል። የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች የብልሆችን ምርጫ መርጠዋል ነው ያሉት።
በሰላም ለሚገቡ ኃይሎችም ምሥጋና አቅርበዋል። ይቅርታ የአሸናፊዎች ምርጫ ነውም ብለዋል። የሰላም አማራጭም የብልሆች ምርጫ መኾኑን ተናግረዋል።
የእስቴ ወረዳ እና የመካነ ኢየሱስ ከተማ ነዋሪዎች እየመከሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የሰላም አማራጭ በማይቀበሉ ኃይሎች ላይ በሚወሰደው ሕግ የማስከበር ርምጃ ተባባሪ እንዲኾኑም ጠይቀዋል።
ጽንፈኞችን ልጆቻችን እንዲማሩ እና ሠርተን እንድንበላ እንፈልጋለን በማለት አቋም ሊይዙ እንደሚገባም ነው ያስረዱት።
የጋራ አቋም በመያዝ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል። ሰላምን በማረጋገጥ ልማትን እንዲያፋጥኑም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን