የዒድ አል አድሃ (አረፋ) ቀን ተግባራት።

12

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ዋነኛው ነው፡፡

የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከሐጅ ሥርዓት ጋር የተያያዘ እንደኾነ የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የዳአዋ እና ትምህርት ዘርፍ ኀላፊ ሼህ መሐመድ ኢብራሂም ይናገራሉ።

የሐጅ ሥነ ሥርዓት ማንኛውም አቅም ያለው ሙስሊም ወደ ጥንታዊት ከተማ መካ በመሄድ ሃይማኖታዊ ተግባራትን የሚፈጽምበት ሥርዓት ነው፡፡

ወደ ጥንታዊቷ ከተማ መካ ለሐጅ የሄዱ የሐጅን ሥነ ሥርዓት ሲፈጽሙ ሐጅ ያልሄዱ በመላው ዓለም የሚገኙ አማኞች ደግሞ የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን በቤታቸው ሲያከብሩ የሚያከናውኑት እያንዳንዱ ተግባር ከነብዩ ኢብራሂም ጋር የሚገናኝ ነው ብለዋል፡፡

ዛሬም ለ1ሺህ 446ኛ ጊዜ የሚከበረው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ምንም አይነት ምግብ ሳይበላ ሴቱም ኾነ ወንዱ ሕጻናት ኾነ የዕድሜ ባለጸጋ ንጹህ በመኾን እና ንጹህ በመልበስ ጥሩ ሽቶ በመቀባት ወደ አደባባይ በመውጣት የዒድ ሰላት ይሰግዳሉ ብለዋል፡፡

ከስግደት መልስም የዕርድ ተግባር ይከናወናል፡፡ ከዒድ ስግደት በኋላ የሚታረደው በግ ለመብል ብቻ ሳይኾን ትልቅ ሃይማኖታዊ እሴት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የሚፈጸመው የዕርድ ተግባር ነብዩ ኢብራሂም እና ልጃቸው ኢስማኤል ለፈጣሪያቸው የነበራቸውን ፍጹም ታዛዥነት ለማስታወስ መኾኑን ነው የነገሩን፡፡

ለበዓሉ ከግመል፣ በሬ፣ በግ እና ፍየል ውጭ ሌላ የእርድ እንስሳት መጠቀም እንደማይቻል የተናገሩት ሼህ መሐመድ ኢብራሂም የሚታረደው ፍየል ከአንድ ዓመት፣ በግ ከኾነ ከስድስት ወር፣ በሬ ከኾነ ከሁለት ዓመት ዕድሜ ማነስ እንደሌለበት እና ግመል ከኾነ ደግሞ የአምስት ዓመት ዕድሜ ሊኖረው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ይህ ዝቅተኛው መጠን እንደኾነ እና ከዚህ በላይ ማረድ እንደሚቻልም ነው የተናገሩት። በዕለቱ ለበዓሉ ተብሎ የሚታረዱ እንስሳት ከሚገዙበት ወቅት ጀምሮ ከፍተኛ ጥንቃቄም ይደረጋል።

ይህ ለአላህ የሚቀርብ ነገር ነውና ያማረና ንጹህ መኾን ስላለበት፤ የጤና እክል ያለበት እንስሳት ለዕርድ አይቀርብም፡ ብለዋል።

ዕርድ የሚፈጸመው ከስግደት በኋላ ነው፤ ከስግደት በፊት ዕርድ የፈጸመ ሰው በዓሉን አስቦ እና አክብሮ ሳይኾን እንደማንኛውም ቀን እንደሚያርደው የሚታሰብ ይኾንበታል ነው ያሉት፡፡

እርዱ ከተፈጸመ በኋላ አንድ ሦስተኛ የሚኾነው ለቤተሰብ፣ አንድ ሦስተኛው ለጎረቤት እና ለዘመድ፤ አንድ ሦስተኛው ደግሞ ለድሆች የሚሰጥ ይኾናል፡፡

ይህ የሚኾነው በበዓሉ ዕለት ስጋ አጥተው ተርበው የሚውሉ እንዳይኖሩ በማሰብ ነው፡፡ የሚታረደው በግ ለመብል ብቻ ሳይኾን ታላቅ ሃይማታዊ ዕሴት እንዳለው ነው የሚገለጸው፡፡

የሚፈጸመው የዕርድ ተግባርም ነብዩ ኢብራሂም እና ልጃቸው ኢስማኤል ለፈጣሪያቸው የነበራቸውን ፍጹም ታዛዥነት ለማስታወስ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

በዓሉ የዘጠነኛው ቀን ጠዋት በስግደት ተጀምሮ እስከ አስራ ሦስተኛው ቀን ማታ አሱር ድረስ ይከበራል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የመሥዋዕትነት እና የመሰጠት በዓል በመኾኑ ሕዝበ ሙስሊሙ በመረዳዳት እና ያለውን በማካፈል ሊያከብር ይገባል”
Next articleይቅርታ የአሸናፊዎች ምርጫ ነው።