
ደብረታቦር: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ ልጫ አሪዳ ቀበሌ የተገነባውን የጉማራ መስኖ ፕሮጄክት መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት እሱባለው መሰለ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ፣ የ303ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ይመር ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች የመስኖ ፕሮጄክቱ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል። አርሶ አደር አበባ ካሴ የግድቡ መሠራት ከአሁን ቀደም ከነበረው ምርት እንድንጨምር ያደርገናል ነው ያሉት።
አርሶ አደር ሙሉጌታ አዳነ ከአሁን በፊት በሞተር እጠቀም ነበር፣ አሁን ግን መስኖው ያለ ምንም ወጭ እንድናለማ ያደርገናል፣ ከውጭ አድኖናል፣ የሠሩትን ሰዎች እናመሠግናለን ብለዋል።
ሌላኛው የአካባቢው አርሶ አደር መዝሙር ሞገስ የመስኖ ፕሮጄክቱ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል። አካባቢው በልማት የታወቀ መኾኑንም ገልጸዋል። የመስኖ ፕሮጄክቱ ከቀደመው የበለጠ እንድናመርት ያደርገናል ነው ያሉት።
በዓመት ሦስት ጊዜ እንዲያለሙ እና በቋሚ ተክልም ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል። አርሶ አደር መልካም ተስፋ ፕሮጄክቱ ትልቅ ጥቅም ይሰጠናል ነው ያሉት።
ከአሁን ቀደምም በጀኔሬተር መስኖ ያለሙ እንደነበር የተናገሩት አርሶ አደሩ ፕሮጄክቱ መሠራቱ ምርታችን እንድንጨምር ያደርገናል ነው ያሉት። ከራሳቸው አልፈው ምርት ለገበያ እንዲያቀርቡ እንደሚያደርጋቸውም ተናግረዋል።
የእስቴ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ማንተፋርዶ ሞላ ፕሮጄክቱ በአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አማካኝነት የተገነባ መኾኑን ገልጸዋል። ለፕሮጀክቱ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበት አንስተዋል።
91 ሄክታር መሬት የሚያለማው ፕሮጄክቱ 153 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል። ማኅበረሰቡ ፕሮጄክቶችን በመጠበቅ እንዲጠቀምበትም አሳስበዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ የአርሶ አደሮችን ዘላቂ ጥቅም ለማረጋገጥ እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል። እስቴ ጽንፈኝነትን አላስተናግድም በማለት ልማቱን አጠናክሮ እየቀጠለ ነው ብለዋል።
ጽንፈኛውን ከአካባቢያቸው በማራቅ ልማታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል። መንግሥት ድህነትን ለማስወገድ በትኩረት እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር የመስኖ ልማት የማይተካ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
የመስኖ ፕሮጄክቱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል። የመስኖ ፕሮጄክቱን እንዲጠብቁ እና በአግባቡ እንዲጠቀሙም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የአካባቢው ሰላም እንዲረጋጋ፣ የልማት ፕሮጄክቶችም ተሠርተው እንዲጠናቀቁ ላደረገው የሀገር መከላከያ እና የክልሉ የጸጥታ ኀይል ምሥጋና አቅርበዋል።
ሕግ ካስከበርን ልማትን ማምጣት እንችላለን ነው ያሉት። ሰላምን እያረጋገጥን ከሄድን ለልማት አንበገርም ብለዋል። መንግሥት ለልማት ቁርጠኝነት እና ጽኑ ዕምነት ስላለው የመስኖ ፕሮጄክቶችን እየገነባ እያስመረቀ መኾኑን ተናግረዋል።
ክልሉ ለመልማት ትልቅ አቅም አለው ያሉት ኀላፊው አርሶ አደሮች ታታሪዎች ናቸው፣ መሬቱም ምቹ ነው ብለዋል። “ክልሉ ያለውን አቅም አሟጥጠን ስንጠቀም ክልሉን እንቀይራለን፣ እድገት እና ብልጽግናን እናረጋግጣለን” ነው ያሉት።
የክልሉ አርሶ አደሮች ታታሪዎች እና የልማት አርበኞች መኾናቸውንም ተናግረዋል። በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾነን በአጭር ጊዜ ፕሮጄክቶችን አስመርቀናል ነው ያሉት ኀላፊው ከዚህ በላይ ሰላም ቢኖር ምን ያክል ልንሠራ እንደምንችል ማሳያ ነው ብለዋል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች በመስኖ ፕሮጄክቱ ዓመቱን ሙሉ መጠቀም እንደሚችሉ እና ምርት እና ምርታማነታቸውን እንደሚያሳድጉ ገልጸዋል። በመስኖ ማኅበር ተደራጅተው በስፋት እንዲያለሙ እና ከራሳቸው አልፈው ለገበያ እንዲያቀርቡም አሳስበዋል።
መንግሥት ሠርቶ አስረክቧችኋል ያሉት ኀላፊው ያለ እረፍት እያመረታችሁ ልማታችሁን ማሳደግ አለባችሁ ብለዋል። በነጻነት እንዲያለሙ እና እንዲያድጉ ጽንፈኞችን መታገል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሕግ ማስከበር ሥራን ከአካባቢው የጸጥታ ኀይል ጋር ኾነው እንዲሠሩም አሳስበዋል። አንድ ኾናችሁ ጽንፈኝነትን ታገሉ አንድ ከኾናችሁ ሰላማችሁን በዘላቂነት ታረጋግጣላችሁ ነው ያሉት።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኀይሎችን እየመከሩ ወደ ሰላም እንዲመልሱም አሳስበዋል። ሰላምን ሲያረጋግጡ ልማት እንደሚረጋገጥም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን