
ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለ1ሺህ 446ኛው የዒድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል አደረሳችሁ ያሉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ በዓሉ በመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው ብለዋል።
የዒድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባለፈ ማኅበራዊ እሴትም ያለው እና ሰዎችን እርስ በእርስ አገናኝቶ የሚያፋቅር በዓል በመኾኑ ልዩ ትርጉም እንዳለው ነው የተናገሩት።
ዒድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል ፍቅርን፣ መልካምነትን፣ መተጋገዝን፣ መተሳሰብን፣ አብሮነትን፣ ለዓላማ ተገዥ መኾንን፣ ታዛዥነትን እና እኩልነት የሚገለጽበት ልዩ በዓል እንደኾነም አስረድተዋል።
በአረፋ በዓል የሃይማኖቱ ተከታዮች የመረዳዳትን እሴት በማጎልበት የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ማሳለፍ እንደሚገባቸው ነው ያስገነዘቡ። የአረፋ አስተምህሮ ከሰላም፣ ከአብሮነት እና ከመከባበር ጋር የሚተሳሰር እንደመኾኑ አማኞች በዚህ እሳቤ በዓሉን ማክበር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
አንድነትን በማጠናከር እና ሰላምን በማጽናት በከተማቸው ልማት ላይ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል። ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ባሕር ዳር ልዩ ልዩ ልማት እያከናዎነች እንደምትገኝ ገልጸዋል። ከዚህም ውስጥ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶቿ እና የኮሪደር ልማቷ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ባሕር ዳር ከተማ ለነዋሪዎቿ ምቹ፤ ለጎብኝወቿ ደግሞ ማራኪ እና ደግመው ደጋግመው የሚመጡባት እንድትኾን እየተሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ምክትል ከንቲባው ይህንንም ማገዝ እንደሚገባ ነው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።
ለባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢዋ ማኅበረሰብ የመስገጃ ቦታ ከተማዋ መስጠቷን ተናግረው አሁንም ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የማስፋፊያ ቦታ ይሰጠን ጥያቄን ለመመለስ እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል።
በአካባቢው ትክ ቦታ የሚያስፈልጋቸውን ትክ ለመስጠት ከተማ አሥተዳደሩ እየሠራ በመኾኑ በቅርብ ጥያቄው መልስ እንደሚያገኝ ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን