የሐጅ እና ኡምራ ጉዞ የሚደረግባት ከተማ- መካ

28

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመካ ከተማ በታሪኳ “መካህ ኣል-ሙከራማህ” ተብላ ትጠራ የነበረች ከተማ ናት። በሳውዲ አረቢያ በስተምዕራብ በኩል ባለው በሒጃዝ ክልል ውስጥ የመካ ክፍለ አውራጃ ማዕከልም ናት።

መካ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ከተማ ተብላ የምትታወቅ ሲኾን የሃይማኖት፣ የታሪክ እና የባሕል ማዕከል እንደኾነች የሚነገርላት ታሪከ ብዙ ከተማ ናት። ከታሪክ አኳያ መካ የነብዩ ሙሐመድ የትውልድ ቦታ እና ቁርዓን መጀመሪያ የተገለጠባት ቦታ እንደኾነችም ይታመናል፡፡

ከተማዋ የታላቁ መስጅድ “አልሐራም” እና በእስልምና ሃይማኖት የተከበረው የ’’ካዕባ’’ መገኛም ናት፡፡ ካዕባ የተገነባው በነብዩ ኢብራሂም እና በልጁ ኢስማኤል እንደኾነ ይነገራል፡፡ መካ ከጥንት ዘመናት ጀምሮ የነበረች ከተማ መኾኗን ጥንተ ታሪኳ ምስክር ነው።

በቁርዓን ውስጥ “ባካ” ተብላ የምትጠራ የነበረ እና ከእስልምና በፊትም የንግድ እና የሃይማኖት እንቅስቃሴ ማዕከል እንደነበረች የሚነገርላት ጥንተዊ ከተማ ናት። ነቢዩ ሙሐመድ የተወለዱበት የቁረይሽ ጎሳ መካን እና ኢኮኖሚዋን የተቆጣጠረ ነበር፤ እነሱም ከእስልምና በፊትም ዓመታዊው የካዕባ የእምነት ተጓዦች በኩል ትልቅ ገቢ ያገኙ ነበር።

የእስልምና ዘመን ተብሎ በሚጠራው ወቅት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ610 ነቢዩ ሙሐመድ በመካ አቅራቢያ ያለው በሒራ ዋሻ ውስጥ የመጀመሪያውን የእስልምና ሃይማኖት መሠረት የኾነውን ቁርዓን ተቀበሉ። ከዚያም በኋላ በእርሳቸው እና በተከታዮቻቸው ላይ ከሚደርሰው ግፍ የተነሳ፣ ከተከታዮቻቸው ጋር በ622 ወደ መዲና ሄዱ። ነገር ግን በ630 ነቢዩ ሙሐመድ እና ተከታዮቹ መካን በኃይል ያስገቡ፤ ካዕባንም ከጣኦቶች አንጽተው እስልምናን በከተማዋ ታዋቂ ሃይማኖት አድርገው መሠረቱ ነው የሚለው የመካ የኋላ ታሪክ።

መካ በመካከለኛው ዘመን ውስጥ የእስልምና ትምህርት እና የሃይማኖት ተጓዦች ማዕከል ኾና የኖረች ከተማ ናት። ከተማዋ በተለያዩ የእስላማዊ ካሊፋቶች ማለትም በመጀመሪያ የዑማያውያን፣ በኋላ የአባሲያውያን፣ ከዚያም የኦቶማን ኢምፓየር መንግሥታት መቆጣጠርን ያስተናገደች ከተማ ናት።

በዘመናዊ የታሪክ ምዕራፏ ላይ እያለች በ1925 ኢብን ሳውድ መካን በኃይል አዲስ ወደ ተቋቋመው የሳውዲ አረቢያ መንግሥት እንድትጠቃለል አድርጓታል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሳውዲ መንግሥት ከፍተኛ የዘመናዊ ልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን ለበለጠ ቁጥር የሃይማኖት ተጓዦች ቦታ እንዲበቃ የመስጂድ አልሐራም ማስፋፊያ ሥራዎችን አጠናክረው ቀጠለው አሁን ላለው ጊዜ መሠረት ጥለዋል።

መካ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ያላት ሚና ሲገለጽ የእስልምና መንፈሳዊ ልብ ናት ማለት ይቻላል። በዓለም ዙሪያ ያሉ ሁሉም ሙስሊሞች ሲጸልዩ የሚመለከቱት አቅጣጫ የኮነችው ‘’ካዕባም’’ መገኛ ናት።

በከተማዋ በየዓመቱ የሚካሄደው የሐጅ ጉዞ ከእስልምና አምስቱ መሠረቶች አንዱ ሲኾን ማንኛውም ችሎታ ያለው አንድ ሙስሊም በሕይዎ ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ መሄድ እንዳአለበት የሃይማኖቱ አስተምህሮ ኾኖ ተቀምጧል።

በተጨማሪም በዓመቱ በማንኛውም ጊዜ ሊከናወን የሚችል የዑምራ ጉዞ ሚሊዮኖችን ለጉብኝት የሚስብ እነ የሚጋብዝም ነው። በመካ ከተማ የሚገኘው መስጅድ አልሐራም በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ስፍራ ሲኾን በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሃይማኖቱ ተከታዮች የሚስተናገዱበት የሃጅና ኡምራ ጉዞ የሚደረግበት ዋና ቦታ ነው፡፡

ካዕባ ማለት ደግሞ በመስጅድ አልሐራም መካከል ላይ ያለች የኩብ ቅርፅ ያላት ቦታ ናት። በእስልምና ውስጥ በጣም የተቀደሰች ቦታ ተደርጋ ትቆጠራለች። የሃይማኖት ተጓዦች በሐጅ እና በዑምራ ሂደት ውስጥ የተካተተ ከካዕባ በዙሪያው በመዞር የሚፈጸም መሠረታዊ ሥርዓት ታዋፍ ተብሎ ይጠራል።

የመስጅዱ ዙሪያ ሰፊ ሲኾን ይህም ለሚሊዮኖች የሚደርሱ ተከታዮች እንዲቀመጡ እና እንዲሰግዱ የተመቸ ነው። መካ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚኖርባት ስትኾን በሕዝብ ብዛቷ በሳውዲ አረቢያ ከሚገኙ ከተሞች ከሪያድ እና ከጂዳ ቀጥላ በሦስተኛነት ተቀምጣለች፡፡ በየዓመቱም በሃጅ እና ዑምራ ጉዞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሃይማኖት ተጓዦችን ታስተናግዳለች፡፡

ምንም እንኳ የሳውዲ አረቢያ ኢኮኖሚ በነዳጅ ሃብት ላይ የተመሠረተ ቢኾንም የሃይማኖት ቱሪዝም በመካ ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦው ጉልህ ነው። የሃይማኖት ተጓዦች ለአካባቢው የንግድ ሥራዎች በተለይም ሆቴሎች፣ የምግብ እና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

በሐጅ ወቅት ብቻ በቢሊዮን ዶላር የሚያመነጭ ገቢ ይገኛል። በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ በመካ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ሴክተር ተብለው የሚጠቀሱት የሆቴል እና መስተንግዶ ተቋማት፣ ንግድ እና የትራንስፖርት ዘርፎች ሲኾኑ በዚህ ጉዞ ቀጥተኛ ተሳታፊ እና ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ በመረጃ ምንጭነት የዓለም ታሪክ እና ሌሎች ድረ ገጾችን ተጠቅመናል።

ዘጋቢ: ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን በባሕር ዳር ከተማ ለማክበር አማኞች ወደ ጋጃ መስክ የዒድ ማክበሪያ ቦታ እየተጓዙ ነው።
Next article1 ሺህ 446ኛው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በደብረ ብርሃን ከተማ እየተከበረ ነው።