የሀጂ ሥርዓት ዓለም ስለእኩልነት ልትማርበት የሚያገባ ጠቃሚ እና ገንቢ እሴቶች ያሉት ነው።

10

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አንድ ወቅት ምድረ በዳ የነበረችው ቅድስቲቷ ምድር መካ የአሏህ ክብር እና ፍቅር ተገልጦባት ሁልጊዜም በየዓመቱ በሚሊዮን በሚቆጠሩ የሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ትዘየራለች፡፡

ሰማዩን እንደ አዕዋፍት ከሰው በላይ ከፍ ብለው እየቃኙ በሚያስመለክቱን የካሜራ ምስሎች ስንመለከተው ካባን የከበበው የበረዶ ክምር እንጂ የሰው ዘር አይመስልም ነበር፡፡ ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ኢስማኤልን እና ባለቤታቸውን ሃጀር ይዘው ያደረጉትን የበርሃ ጉዞ 632 ዓ.ም ላይ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ዳግም ተጓዙት፡፡ የሀጂ ሥርዓት በዚህ መልኩ ተጀመረ፡፡

በዓረፋ በዓል የሀጂ ሥርዓትን ለመፈጸም ወደ ቅድስቲቱ ምድር መካ መዲና የሚጓዙ የሃይማኖቱ ተከታዮች በቆይታቸው የተለያዩ ቦታዎችን ይጎበኛሉ፡፡ ከመካ ወደ መዲና፣ ከዓረፋ ወደ ሙዝደሊፋ፣ ከሚና ወደ ጀማረፋት፣
ከሚና ወደ መካ እየተንቀሳቀሱ ምስጋና ያቀርባሉ፡፡

የዘር ሃረግ፣ የቆዳ ቀለም፣ ምጣኔ ሃብታዊ ደረጃ፣ የመደብ ልዩነት እና ሥልጣን ሳይገድባቸው በአሏህ ፊት እኩል የሚኾኑበት ሥርዓት ነው፤ የሀጂ ሥርዓት፡፡ ከሁሉም የዓለም ክፍሎች የተሠባሠቡት አማኞች በዚያች ቅድስት ከተማ ከቅዱስ ተግባራት እና ምሥጋና ውጭ ከአፋቸው እንኳን ክፉ አይወጣም፡፡

ያሰባሰባቸው የአሏህ እዝነት እና ርህራሄ ነውና “አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ” ከመባባል ያለፈ ክፉ ነገር ፈጽሞ የለም፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማኞች በሚሠባሠቡባት በዚያች ጠባብ የካባ ሥፍራ ለሰላት እንኳን በአንድ ጥሪ ብቻ ቦታ ቦታቸውን ይዘው ለስግደት ይዘጋጃሉ፡፡

በዒድ አል አድሃ በዓል ከሚፈጸሙ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዱ ሀጂ ማድረግ ነው፡፡ ሀጂ ማድረግ የእስልምና ሃይማኖት ከቆመባቸው አምስት ምሰሶዎች መካከል አንዱ ነው ይላሉ ሼህ አብዱራሂም ሙሳ፡፡
አንድ ሙስሊም በሕይዎት ዘመኑ ሊያሳካቸው ከሚፈልጋቸው ሃይማኖታዊ ምኞቶች መካከል ቀዳሚው ሀጂ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ሀጂ ሳደርግ የተሰማኝን የደስታ ስሜት ያክል ደስታን አጣጥሜ አላውቅም የሚሉት ሼህ አብዱራሂም በቁራኣን የተማርናቸውን፣ በሃይማኖት አስተምህሮ መጻሕፍት ያነበብናቸውን እና ከታላላቆቻችን የሰማናቸውን ቅዱስ ቦታዎች መመልከት የተለየ ስሜት ይሰጣል ይላሉ፡፡

“የሀጂ ሥርዓት ዓለም ስለእኩልነት ልትማርበት የሚያገባ ጠቃሚ እና ገንቢ እሴቶች ያሉት ነው” የሚሉት ሼህ አብዱራሂም መከባበሩ፣ መቻቻሉ እና አንድነቱ ፍጹም የተለየ ስሜትን የሚሰጥ ነው ይላሉ፡፡ “ሀጂ ማድረግ በምድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነባችውን የአሏህን ቤት መጎብኘት ነው” የሚሉት ሼህ አብዱራሂም ካእባን ሰባት ጊዜ ሙሉ እየዞሩ ማመስገን ምን አይነት የደስታ ስሜት ይፈጥራል ብትለኝ መግለጽ ይከብዳል ይላሉ፡፡

ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጉዞ በኋላ አካላዊ አቅማቸው፣ ጤንነታቸው እና የገንዘብ አቅሙ የፈቀደላቸው የሃይማኖቱ ተከታዮች ሁሉ በሕይዎት ዘመናቸው አንድ ጊዜ ሀጂ እንዲያደርጉ ያስገድዳልም ይላሉ፡፡ በመካ በሚገኘው ታላቁ መስጂድ እምብርት ላይ ያለው ጥቁር ሀር ለበስ ካባ በነቢዩ ኢብራሁም እና በልጃቸው እስማኤል የተገነባ ነው። በዚህ መስጂድ ዙሪያ ያለው የሀጃጆች ውበት እና ሙሃባ የተለየ ነው፡፡

ሀጂ የልዩነትን በር አጥብቦ የአንድነትን፣ የመተሳሰብን እና የአብሮነትን መንገድ የሚከፍት ነው የሚሉት ሼህ አብዱራሂም የሀጅ ዋና ዓላማውም አንድነትን ማጽናት ነው ብለዋል፡፡ ሀጅ አስተምህሮው ጥልቅ፣ ምሥጢሩ ረቂቅ እና ፋይዳው ትልቅ ነው የሚሉት ሼህ አብዱራሂም እኛ የአሏህ እንግዶች ነን፤ የአሏህ እንግዶች ደግሞ የፈጣሪያቸውን ቤት መጎብኘታቸው ብዙ እንዲያተርፉ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡

እኔ በመሀጀጄ ብዙ አትርፌያለሁ፤ ሌሎችም ያ ሙሃባ እንዲደርሳቸው እመኛለሁ ነው ያሉት፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች በተሳካ መልኩ እንዲከናወኑ ባለድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።