የክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች በተሳካ መልኩ እንዲከናወኑ ባለድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

18

ደብረ ማርቆስ: ግንቦት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተና አሰጣጥን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አድርጓል፡፡

የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል የክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች በተሳካ መልኩ እንዲከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ያምራል ታደሰ ተናግረዋል፡፡ በከተማ አሥተዳድሩ በ2017 የትምህርት ዘመን ከ4 ሺህ 800 በላይ ተማሪዎች ክልል አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን እንደሚወስዱ መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል፡፡

በየደረጃው የሚሰጡ ፈተናዎች የፈተና ደንብ እና ሥርዓትን በተከተለ መልኩ በአግባቡ መሰጠት ይኖርባቸዋል ያሉት መምሪያ ኀላፊው ፈተናዎቹ ሰላማዊ በኾነ መንገድ እንዲጠናቀቁ ከቅድመ ዝግጅት ተግባራት እስከ ማጠቃለያ ምዕራፍ ድረስ ባለድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ስለሺ ተመስገን በውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያለፉም ቢኾን መምህራን እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተማሪዎችን ለክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ለማዘጋጀት ያሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋና የሚቸረው መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች ራሳቸውን ለፈተና ዝግጁ እንዲያደርጉ መደገፍ እና ሥነ ልቦናቸውን መገንባት ከትምህርት ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ሳይስተጓጎሉ በአግባቡ እንዲከናወኑ የጸጥታ ኀይሎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ያነሱት ምክትል ከንቲባው የክልል እና የሀገር አቀፍ ፈተናዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ ሙያዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡ ርእሳነ መምህራን ተማሪዎች በተረጋጋ መንገድ ፈተናዎችን እንዲፈተኑ ለማድረግ በሥነ ልቦና ዝግጁ የማድረግ እና አስፈላጊው የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሞዴል ፈተናዎች ጀምሮ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማከናወናቸውንም የትምህርት ቤት ርእሳነ መምህራን ነግረውናል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጤናማ አካባቢ ለመፍጠር በቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ላይ ሁሉም ሊሠራ ይገባል።
Next articleየሀጂ ሥርዓት ዓለም ስለእኩልነት ልትማርበት የሚያገባ ጠቃሚ እና ገንቢ እሴቶች ያሉት ነው።