የወረርሽኙ ሥርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አማካሪ ግብረ ሃይሉ አስታወቀ፡፡

144

 

ባሕርዳር፡ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) የሚኒስትሮች ኮሚቴ ከኮሮናቫይረስ መከላከል አማካሪ ግብረ-ሃይል ጋር በወቅታዊ የወረርሽኙ ስርጭት እና መከላከል ዙሪያ ዛሬ ተወያይቷል፡፡

ውይይቱን የመሩት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የወረርሽኙ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እና አሳሳቢነቱ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የፀረ-ኮሮናቫይረስ እንቅስቃሴ በትኩረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ የችግሩን አስከፊነት ከግምት ያስገቡ የጥንቃቄ ርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል አማካሪ ግብረ-ሃይል አባላት በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚስተዋለው የወረርሽኙ ስርጭት ፍጥነቱ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመላው ሃገሪቱ ከተመረመሩት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ከአዲስ አበባ መሆናቸውን በመጥቀስም በመዲናዋ ወረርሽኙ በአሳሳቢ ደረጃ ስርጭቱ እየጨመረ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የወረርሽኙ ስርጭት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የሚወሰን ባለመሆኑ ኅብረተሰቡ የጥንቃቄ ርምጃዎችን ሳይዘናጋ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበትም የአማካሪ ግብረ ሃይሉ አባላት አሳስበዋል፡፡

መላው ኅብረተሰብ የወረርሽኙን ስርጭት አሳሳቢነት በመገንዘብ እጅን በየጊዜው በመታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን ጠብቆ በመንቀሳቀስ እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በመጠቀም ወረርሽኙን እንዲከላከልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የምርመራ ሥራው እንዲጠናከርና ችግሩን የሚመጥን የህግ ማስከበር ሥራ ተግባራዊ እንዲደረግም የአማካሪ ግብረ ሃይሉ አባላት መክረዋል፡፡

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ስልጠና ተሰጥቷቸው ኅብረተሰቡን በማስተማር ሥራ እንዲሰማሩ ደግሞ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አቅጣጫ ማስቀመጡን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Previous articleየኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቅድመ መከላከል ሥራ መቀዛቀዙ እንዳሳሰባቸው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
Next articleየትግራይ ሕዝብ ለነጻነት እና እኩልነት የሚያደርገውን ትግል እንደሚደግፍ አብን አስታወቀ፡፡