ጤናማ አካባቢ ለመፍጠር በቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ላይ ሁሉም ሊሠራ ይገባል።

14

ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም የአካባቢ ቀን በዓለም ለ52ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ32ኛ፣ በአማራ ክልል ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ “የፕላስቲክ ብክለትን እንግታ” በሚል መሪ መልዕክት በክልሉ ከግንቦት 19/2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በዛሬው ዕለትም የማጠቃለያ ውይይት በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። የፕላስቲክ ብክለት በአካባቢ ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽዕኖ የሚያሳዩ ጥናቶችም ቀርበዋል። የአማራ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ በልስቲ ፈጠነ ለዱር እንስሳት ምቹ የኾነ አካባቢ ለመፍጠር የአካባቢ ጥበቃ ዘላቂነትን የማረጋገጥ፣ የደን ሀብትን የመጠበቅ እና የማልማት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የተፈጥሮ ደኖችን፣ ብሔራዊ ፓርኮችን እና የማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራዎችን የመጠበቅ እና የማልማት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት። ይኹን እንጂ የደረቅ እና የፍሳሽ ቆሻሻዎች አወጋገድ ችግር በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል ነው ያሉት።

በተለይም የፕላስቲክ አጠቃቀም እና አወጋገድ ችግር ፈታኝ መኾኑን ነው የገለጹት። ችግሩ የሰውን ልጅ ጤናማ በኾነ አካባቢ የመኖር መብትን የሚነፍግ መኾኑን ገልጸዋል። ንጹህ እና ጤናማ አካባቢ ለመፍጠር ደግሞ አካባቢን በመጠበቅ፣ በማልማት እና በቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ላይ ሁሉም ኀላፊነት ወስዶ ሊሠራ ይገባል ብለዋል ምክትል ኀላፊው።

አካባቢን በሚበክሉ እና በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ጉዳት በሚያደርሱ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል። የናቡ ኢትዮጵያ ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አቅም ግንባታ አማካሪ ባይህ ጥሩነህ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱ በኢኮኖሚ፣ በጤና፣ በከርሰ ምድር ውኃ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። የፕላስቲክ ብክለት አሳሳቢ እየኾነ መምጣቱን ነው የገለጹት።

አማካሪው እንዳሉት የፕላስቲክ ብክለትን ለመከላከል ናቡ ኢትዮጵያ በባሕር ዳር እና ጎንደር መልሶ መጠቀም ላይ እየሠራ ይገኛል። ማኅበረሰቡ የሚበሰብሱ እና የማይበሰብሱ ቆሻሻዎችን ቤት ላይ እንዲለይ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል። የሚበሰብሰውን ቆሻሻ ለግብርና ሥራ እንዲውል ወጣቶችን በማደራጀት በኮምፖስት ዝግጅት እንዲሠማሩ ተደርጓል።

በቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱ ማኅበረሰቡን ለማሳተፈ ከአጋር አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የፕላስቲክ አጠቃቀምን ለማስተካከል አማራጮችን በተመጣጣኝ ዋጋ በስድስት ከተሞች ለሚገኙ የመሸጫ ሱቆች እያቀረቡ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይ በሌሎች ከተሞች ለማስፋት መታቀዱን አንስተዋል።

የአይቸው፣ ሜሮን እና ጓደኞቹ የሃይላንድ ሳይክል ማኅበር አባል የኾነው አይቼው ደባስ ደግሞ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በከተማው የሚገኘውን ደረቅ ቆሻሻ በመፍጨት ለፋብሪካዎች እያቀረቡ ይገኛል። ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ 15 ሚሊዮን 566 ሺህ 625 “የሃይላንድ”ፕላስቲኮችን በመፍጨት ለፋብሪካዎች ማቅረባቸውን ለአብነት አንስተዋል።

ማኅበሩ ከባሕር ዳር ባለፈ በተለያዩ ወረዳዎች ጭምር የሃይላንድ ፕላስቲኮችን እየበሰበሰ መኾኑን ገልጸዋል። ለ15 ሰዎችም የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ነው የገለጹት።

ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleኢትዮጵያ በመልካም የእድገት ጎዳና ላይ መኾኗን የስሎቬኒያ ፕሬዝዳንት ናታሽ ፒርስ (ዶ.ር) ተናገሩ።
Next articleየክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች በተሳካ መልኩ እንዲከናወኑ ባለድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።