
አዲስ አበባ: ግንቦት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የስሎቬኒያ ፕሬዝዳንት ናታሽ ፒርስ (ዶ.ር) የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን ጎብኝተዋል።
ፕሬዚዳንቷ በጉብኝታቸው ወቅቱ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ቅርሶችን እና ታሪክን መጠበቅ የትውልድ አደራ መኾኑንም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ የአስደናቂ ታሪክ ባለቤት መኾኗን ያወሱት ፕሬዝዳንቷ የባሕል ተቋማት ይሄን ታሪክ ለመልካም ተሞክሮ እንዲጠቀሙበት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
አዲስ አበባ እንደገቡ በርካታ ግንባታዎችን እና የልማት እንቅስቃሴዎችን እንደተመለከቱ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ናታሽ ፒርስ (ዶ.ር) ይሄም ኢትዮጵያ በመልካም የእድገት ጎዳና ላይ የመኾኗ ምልክት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ አበባ የዓለም ዲፕሎማሲያዊ ከተማ ተብላ የምትታወቅ መኾኗን ገልጸው፣ ስሎቬኒያ በቅርቡ ኤምባሲ በመክፈቷ በከተማዋ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና ካላቸው ሀገራት አንዷ ትኾናለች ብለዋል።
የኢትዮጵያን የወደ ፊት እድገት ለመደገፍ የስሎቬኒያ ልማት ፈንድ የሚያደርግባቸው ቦታዎችን ማየትም የጉብኝታቸው አካል መኾኑን ገልጸዋል።
ስሎቬኒያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጊዜዓዊ አባል መኾኗን የተገለጹት ፕሬዝዳንቷ ከዚህ ጋር ተያይዞ አፍሪካ በተደጋጋሚ በጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ላይ የምትጠቀስ በመኾኗ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዝደንት ጋር ውይይት እናደርጋለንም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን