“ሕዝብ በአንድነት ሲነሳ የማያሸንፈው ጠላት የለም” አቶ ይርጋ ሲሳይ

9

ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ከአንዳቤት ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል። የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የአንዳቤት ወረዳ ሕዝብ ትርፍ አምራች እና ያመረተውን ሌሎችም የሚያቀርብ ጀግና ሕዝብ ነው ብለዋል። በአካባቢው መንግሥት የጀመራቸው ትልልቅ የልማት ሥራዎች እንዳሉም ተናግረዋል።

ከጎጃም ጋር የሚያገናኝ ትልቅ መንገድ ተጀምሮ እንደነበር የተናገሩት ኀላፊው መንገዱ በጥሩ ኹኔታ እየሄደ ባለበት ወቅት በተራ ወንበዴዎች ምክንያት እንዳይጠናቀቅ ኾኗል ነው ያሉት። ለመንገድ ሥራው አገልግሎት ላይ የነበሩ ማሽኖች መዘረፋቸውንም አንስተዋል። ይህ ደግሞ አሳፋሪ እና አስነዋሪ ተግባር ነው ብለዋል። መንገዱ እንዳይጠናቀቅ ያደረጉ እና ማሽኖችን የዘረፉት ከሌላ አካባቢ አልመጡም ነው ያሉት።

የአንዳቤት አካባቢ ሲያርስ፣ ሲያመርት እና እንግዳ ሲቀበል የሚያምርበት እውነተኛ ሕዝብ ነው ያሉት ኀላፊው ለእናንተ የማይኾነውን ቡድን ማስወገድ ይገባችኋል ብለዋል። በቆየ ጀግንነታችሁ ሰላማችሁን ካስጠበቃችሁ የመልማት ጥያቄዎቻችሁ ደረጃ በደረጃ ይፈታሉ ብለዋል። ሰላምን ከጠበቁ የማዳበሪያ አቅርቦት በተገቢው መንገድ እንደሚደርስም ገልጸዋል።

በወንበዴው ቡድን ልባችሁ እንደተሰበረ እና እንደተሰቃያችሁ ተረድተናል ያሉት ኀላፊው ሕጻናት አይማሩም ባለ ጊዜ ትውልድን ለማቋረጥ እንደተነሳ ተረድተናል ብለዋል። ጽንፈኛ ቡድኑ በሕዝብ ላይ ያላደረገው ነገር እንደሌለም ተናግረዋል። ኩሩው፣ ትልቁ፣ አስታራቂው እና አስታዋዩ የአንዳቤት ሕዝብ ጽንፈኞችን መክሮ መመለስ አለበት ብለዋል።

ልጆች ከትምህርት ገበታ ሲርቁ፣ በሕዝብ ላይ መከራ ሲበዛ ለምን ዝም አላችሁ? ነው ያሉት። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች መክረው እና ገስጸው ሰላም እንዲመጣ እንዲያደርጉም አሳስበዋል። ሕዝብ በመከራ ውስጥ ወድቆ የታሪክ ተወቃሽ እንዳትኾኑ የሚጠበቅባችሁን ተወጡና ሕዝብን ከስቃይ አድኑ ብለዋል።

የመንግሥት ሠራተኞች ሕዝብን በተገቢው በማገልገል እና ጽንፈኛውን በመታገል ለሕዝብ ውለታ እንዲውሉም ጠይቀዋል። ችግሩን ከወዲሁ መቋጨት ካልተቻለ በሁሉም ቤት እንደሚገባም ገልጸዋል። የአካባቢው ወጣቶች ከጽንፈኝነት አስተሳሰብ ለመራቅ እያደረጉት ላለው መልካም ተግባር ምስጋና አቅርበዋል። አኹንም በአንድነት ተነስተው የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲያስከብሩ አሳስበዋል።

ጽንፈኛው ወደ ጫካ የገባው ለራሱ ጥቅም ነው ያሉት አቶ ይርጋ ሲሳይ ለአማራ ሕዝብ የሚጠቅም ሃሳብ እንደሌላቸው እና የሕዝብን ሃብት መዝረፋቸውን ነው የተናገሩት። በጫካ የገቡ ኃይሎች ወደ ሰላም ይምጡ በሰላም እንቀበላቸዋለን፣ መንግሥት ይቅር ይላል፣ መክራችሁ፣ ዘክራችሁ አምጧቸው ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአድማ መከላከል፣ ለሰላም አስከባሪ እና ለሚሊሻ ትልቅ ክብር ይገባቸዋልም ብለዋል። በመስዋዕትነት ሰላምን እያስከበሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የሰላም አማራጩን በማይጠቀሙ ኃይሎች ላይ ግን ሕግ የማስከበር እርምጃው ይቀጥላል ያሉት ኀላፊው የሕግ ማስከበር ሥራውን እንዲያግዙም አሳስበዋል። “ሕዝብ በአንድነት ሲነሳ የማያሸንፈው ጠላት የለም፤ ይህ ታሪካችን ይመሰክራል” ነው ያሉት። በሰላም ከመጡ በሰላም እንቀበላለን፣ እንቢ ካሉ ግን ሕግ ይከበራል ብለዋል።

የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲቀጥሉ፣ ያልተጀመሩት እንዲጀመሩ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች እንዲመጡ ማድረግ እንደሚገቸውም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል ሲያከብር የተቸገሩትን በማሰብ ሊኾን እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ።
Next articleኢትዮጵያ በመልካም የእድገት ጎዳና ላይ መኾኗን የስሎቬኒያ ፕሬዝዳንት ናታሽ ፒርስ (ዶ.ር) ተናገሩ።