ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል ሲያከብር የተቸገሩትን በማሰብ ሊኾን እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ።

14

ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓልን ሲያከብር የተቸገሩትን እና የተፈናቀሉትን በመርዳት፣ የታመሙትን በመጠየቅ እና በማሳከም መኾን እንዳለበት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳስቧል።

ዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) ክብረ በዓል የዕርድ በዓል ተብሎም ይታወቃል ያሉት በአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የዳዕዋ እና የትምህርት ዘርፍ ኀላፊ ሼህ መሐመድ ኢብራሂም በዓሉ የሰላም፣ የአንድነት እና የብለጽግና እንዲኾን ተመኝተዋል።

ሼህ መሐመድ አያይዘውም የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል የሚከበረው በነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ትዕዛዝ መኾኑን ተናግረዋል። ይኸውም ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን ሐጀር ከምትባለው ባለቤታቸው ከወለዱ በኋላ በመካ እንዲያድግ መደረጉንም ሼህ መሐመድ አውስተዋል።

ልጁ (እስማኤል) መካ ላይ እያለ ዕድሜው 13 ነበር ያሉት ሼህ መሐመድ ሌላ መልዕክት ከአሏህ እንደመጣም ተናግረዋል። መልዕክቱም “ልጅህን ዕረድ” የሚል ከባድ እና አሳዛኝ እንደነበር ጠቁመዋል። የጌታ ትዕዛዝ ባይኾን ኑሮ ማንም አያደርገውም ነበር። ምክንያቱም ልጁ የተገኘው በብዙ ጭንቀት፣ ድክመት፣ ልፋት እና ጸሎት ነበርና ነው ያሉት። የእርሳቸው እድሜም (የነብዩ ኢብራሂም) ከ80 ዓመት በላይ ነበር ብለዋል።

በስስት እና በጉጉት የሚያዩት ልጅ አድጎ፣ ለሥራ ብቁ በሚኾንበት ሰዓት ነው “አሏህ ልጅህን ዕረድ” ያላቸው ሲሉ ሼህ መሐመድ ተናግረዋል። ነብዩ ኢብራሂምም የአሏህን ትዕዛዝ ተቀብለው ልጃቸውን ፈጥነው ልረድህ ከማለት፤ “ልጄ ኾይ! ከአሏህ ዘንድ አንተን እንዳርድ ትዕዛዝ መጣ። ምን ይመስልሃል?” እንዳሉት ሼህ መሐመድ አብራርተዋል።

ልጁም በቅንነት እና በታማኝነት “የእኔን ነፍስ ከአሏህ ትዕዛዝ ልታበልጥ አይገባኽም። እነኾ የጌታህን ትዕዛዝም ፈጽም። እኔም ለመታረድ ዝግጁ ነኝ አላቸው” ብለዋል። ነብዩ ኢብራሂም ከልጃቸው ፍቃድ በማግኘታቸው ካራቸውን ሥለው ልጁን አንጋለው አንገቱ ላይ ሊያሳርፉ ሲሉ ከአሏህ በኩል ሌላ ጥሪ መምጣቱን አስታውሰዋል።

“አንተ ኢብራሂም ኾይ! እውነት ነው፤ አንተ ትዕዛዝህን በእርግጠኝነት ለመፈጸም መዘጋጀትህን አረጋግጠናል። እነኾ! በልጁ ፈንታ ይሄን ሙክት ለአንተ ተችሮሃል። በልጁ ፈንታ ፊዳ (መስዋዕት) ይህን ሙክት እረድ ብሎ አሏህ አዘዘ። ነብዩ ኢብራሂምም ሙክቱን ተቀብለው አረዱ ነው ያሉት ሼህ መሐመድ።
የዚህ አስተምህሮም መቀጠሉን እና ወደ ፊትም እንደሚቀጥል የዳዕዋ እና የትምህርት ዘርፍ ኀላፊው ሼህ መሐመድ ገልጸዋል።

ነብዩ ኢብራሂምም ሙክቱን ሲያርዱ ለዑማዎች ጠበቅ ያለ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ይኸውም “የሚያርዷቸውን ፍየሎች፣ በጎች፣ ከብቶች እንከን የሌለባቸው መኾን ይገባቸዋል። ሲታረዱ ከራስ ባለፈ ሌሎችንም ምስኪኖች ታሳቢ ማድረግ ግድ ነው። የሚታረደውም ለሦስት ተከፍሎ አንድ ሦሥተኛው ለጎረቤት ይሰጣል። አንድ ሦሥተኛው ለምስኪኖች ይለገሳል። አንድ ሦሥተኛው የራስን እንግዳ ማስተናገጃ ይውላል” ነው ያሉት።

ሼህ መሐመድ የዒድን በዓል አስመልክተው እንዳሉት ሰዎች በዚች ዓለም ላይ ስንኖር አንዱ ደልቶት ሌላው ከፍቶት፤ አንዱ በቤቱ ሌላው ተፈናቅሎ ይኖራል። ስለኾነም የዒድ በዓልን ስናከብር የተቸገሩትን፣ የተፈናቀሉትን በመርዳት፣ የታመሙትን በመጠየቅ እና በማሳከም መኾን አለበት ነው ያሉት።

በጎ ነገር መሥራት የበዓሉ ቅድመ ኹኔታ እንደኾነም አስገንዝበዋል። ደግነት ሰዋዊም ነው ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች ሰርክ ሰላምን በመስበክም ተከታዮቻችን ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ ማድረግም ይገባናል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleኢትዮጵያ እና ስሎቬንያ ሪፐብሊክ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።
Next article“ሕዝብ በአንድነት ሲነሳ የማያሸንፈው ጠላት የለም” አቶ ይርጋ ሲሳይ