“ለሁሉም ነገር ሰላም ያስፈልጋል” የአንዳቤት ወረዳ ነዋሪዎች

34

ደብረ ታቦር: ግንቦት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከደቡብ ጎንደር ዞን አንዳቤት ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት እሱባለው መሰለ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የታጠቀው ኃይል በሕዝብ ላይ መከራ እያደረሰ ነው ብለዋል። በየደብሩ እየተመላለሱ አርሶ አደሮችን እያሰቃዩ፣ ገንዘብ በግዴታ እየተቀበሉ እምቢ ያሉት እየተደበደቡ ነው፣ መንግሥት እንዲደርስልን እንፈልጋለን ነው ያሉት።

ልጆቻችንን እንዳናሳድግ አድርገውናል ብለዋል። የሕዝብ ሃብት እየዘረፉ ሃብታቸውን እያካበቱ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የሕዝብን ንብረት እየዘረፉ ሃብት የሚያካብቱ ሰዎችን መንግሥት የተጠናከረ እርምጃ ሊወስድባቸው ይገባል ነው ያሉት። እኛም እናግዘዋለን ብለዋል።

በአንዳቤት እና በአዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ የታጣቂ ቡድኑ መመሸጊያ ሥፍራዎችን በተቀናጀ ኃይል መምታት እንደሚገባም ገልጸዋል። መከላከያ እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል እርምጃ ሊወስዱ ሲሄዱ መረጃ አስቀድሞ የሚያወጣ ኃይል እንዳለም ገልጸዋል።

በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች አስነዋሪ ተግባር እየፈጸሙ መኾናቸውን ተናግረዋል። ለሰላም ግቡ ብለን ስንመክር፣ ስብሰባ ውለን ስንሄድ እስኪ መንግሥት ይድረስላችሁ እየተባልን እየተሰቃየን ነው ብለዋል።

ልጆቻችን እና ንብረታችን የምንጠብቅበትን ሕጋዊ መሣሪያ እየነጠቁ ወስደውብናል ነው ያሉት። ሰላም ያስፈልጋል ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች አርሶ ለመብላት፣ እልል ብሎ ለመዳር፣ አልቅሶም ለመቅበር ሰላም ሊኖር ይገባል ነው ያሉት።

ለአካባቢው የማዳበሪያ አቅርቦት በሥፋት እንዲደርስም ጠይቀዋል። የመብራት እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱላቸውም አንስተዋል።

የ303ኛ ኮር አዣዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተሾመ ይመር የሰላም እጦት ሕዝብን ለከፍተኛ ችግር እየዳረገ መኾኑን ተናግረዋል። የአካባቢው አርሶ አደሮች በራሱ ልጆች ተሸማቅቆ እንዲኖር፣ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ፣ አምርቶ እንዳይበላ መደረጉን ገልጸዋል።

ሕዝብን እያሰቃዩ ያሉ የጥፋት ኃይሎችን እየመከሩ መመለስ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በራሳቸው ሕዝብ ላይ መከራ እና ስቃይ እያደረሱ መኾናቸውንም አንስተዋል። የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ከልብ ከሠራችሁ ግጭቱ ያቆማሉ ብለዋል።

በሰላም የሚመጡት በሰላም እንዲመጡ፣ በሰላም የማይገቡትን ደግሞ አሳልፋችሁ መስጠት አለባችሁ ነው ያሉት። ሕዝብን እያሰቃዩ ያሉ የጥፋት ኃይሎችን እንዳያበሉ እና እንዳያጠጡም አስገንዝበዋል። ልማት እንዲመጣ ከተፈለገ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል። እናንተ ፊታችሁን ካዞራችሁባቸው አንድ ቀን ውለው ማደር አይቻላቸውም ነው ያሉት።

የጥፋት ኃይሎችን መደገፍ ማቆም አለባችሁ ያሉት አዛዡ ከመከላከያ እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ጋር አብራችሁ ሥሩ፣ ይሄን ካደረጋችሁ በአጭር ጊዜ ሰላም ይረጋገጣል ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ የአርበኝነት ሥራ ሠርታችሁ ሰላማችሁን ማስከበር አለባችሁ ብለዋል። የሚዘርፋችሁን፣ የሚደበድቧችሁን፣ ልጆቻችሁ እንዳይማሩ የሚከለክሏችሁን በአንድነት ተነስታችሁ መከላከል አለባችሁ ነው ያሉት።

በአንድነት ተነስተው በአጭር ጊዜ ከወረዳቸው እንዲያጸዱም አሳስበዋል። እንዳታመርቱ ይከለክሏችኋል፣ የያዛችሁትን ጥሪት ደግሞ ይነጥቋችኋል፣ ታዲያ እነዚህን እስከመቸ ነው የምትጠብቁት ነው ያሉት።

ዓላማ የሌለውን ቡድን በጋራ በመነሳት ማጥፋት እና አሳልፋችሁ መስጠት አለባችሁ ብለዋል። በአንድነት ተነስታችሁ ከታገላችሁ በአጭር ጊዜ ሰላም ይረጋገጣል ነው ያሉት።

ማብላት ማጠጣታችሁን እስካልከለከላችሁ ድረስ ግፉ እና በደሉ ይቀጥላል ብለዋል። በአንድነት ተነስታችሁ በቃን ካላችሁ ግን ሰላማችሁ በአጭር ጊዜ ይመለሳል ነው ያሉት። የልማት ሥራዎችን እንዳይሠሩ የሚያደርጉ ጽንፈኞች መኾናቸውን ነው የተናገሩት። የልማት ሥራዎች እንዲሠሩ ጽንፈኞችን እንዲታገሉም አሳስበዋል። የማዳበሪያ አቅርቦት በስፋት እንዲመጣ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleእንኳን ለ1446ኛው የአረፋ(ዒድ አል አድሃ) በዓል አደረሳችሁ
Next articleኢትዮጵያ እና ስሎቬንያ ሪፐብሊክ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።