
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ አካባቢ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 12 ታጣቂዎች መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከነሙሉ ትጥቃቸው ገብተዋል።
እራሱን “የኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ ብርጌድ” ብሎ ከሚጠራው የታጣቂ ቡድን አባላት መካከል፦
1. ሻምበል መንግሥቱ ድልነሳ ዓለም – ሻለቃ አዛዥ
2. መቶ አለቃ ምስጋናው ሽታ ገረመው – ሻለቃ ዘመቻ ኀላፊ
3. ዶክተር አንለይ አሰፋ ዘላለም – በአቸፈር ቀጠና አቤ ጎበኛ ብርጌድ አስተዳደር እና ጸጥታ ኀላፊ ጨምሮ ሌሎች 8 አመራሮች እና አባላት መንግሥት የሰጣቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ገብተዋል።
በአቀባበሉ ላይ የሰሜን ጎጃም ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኀላፊ ገብረስላሴ ታዘብ፣ የምስራቅ ዕዝ ኮር አመራሮች፣ የመርዓዊ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ብርሃኑ አበረ፣ የመርዓዊ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌታነህ መልኬ ተገኝተዋል።
የሰላም ጥሪውን የተቀበሉት ታጣቂዎች እስካሁን የሄድንበት መንገድ የተሳሳተ ነበር ብለዋል። በተሳሳተ መንገድ ተጉዘን ቤተሰቦቻችን እና መላ ሕዝባችን ብዙ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርገናል ያሉት ታጣቂዎቹ በሂደቱም ብዙ ወንደሞቻችን እና እህቶቻችን አጥተናል ነው ያሉት።
ተጨማሪ የሕይዎት መስዋዕትነት መከፈል የለበትም። ነገ ድርድር ቢደረግ የማናገኛቸውን ወጣቶች ማጣት የለብንም ብለን የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን የሕዝባችንን መከራ ለማቆም ወስነን የሰላም ጥሪውን ተቀብለናል ብለዋል።
አሁንም በተሳሳተ መንገድ ላይ ያሉ ወንድሞቻችን የእኛን ፈለግ ተከትለው መንግሥት የዘረጋው የሰላም ጥሪ ሊቀበሉ ይገባል። የሕዝብ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ የሚቀርብባቸው መንገዶች አሉ ያሉት ታጣቂወቀቹ ተጨማሪ የሕይዎት መስዋዕትነት የምንከፍልበት መንገድ ግን ሊቋጭ ይገባል ማለታቸውን ከምስራቅ ዕዝ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!