47ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች፦

32

ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 47ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው የ2018 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ የበጀት አዋጅ ላይ ነው፡፡ የ2018 ዓ.ም የፌዴራል መንግሥት በጀት በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈጸም፤ የሀገር ደህንነትን ከማስጠበቅ፣ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ፣ በተፈጥሮና ሠው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመርዳት አንጻር፤ የ2018-2022 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍን መሠረት በማድረግ እና የ2017 በጀት ዓመት የፕሮግራም በጀት አፈጻጸምን በመገምገም ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው፡፡

በዚሁ መሠረትም ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎች፣ ለካፒታል ወጪዎች፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ወደ ሁለት ትሪሊዮን የሚጠጋ በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው የፌዴራል መንግሥት የ2018 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. ሌላኛው ምክር ቤቱ የተወያየበት በስታርታፕ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የስታርታፕ ምህዳርን በመፍጠር ስታርታፖች የሚመሰረቱበት፣ የሚንቀሳቀሱበትና የሚያድጉበት እና ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ አዳዲስ ምርቶችን የሚያመርቱበትና አገልግሎቶችን የሚሰጡበት እንዲኹም በዘርፉ የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት እንዲያስችል ኾኖ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በአዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሮቢንሁድ ራንሰምዌር
Next articleበሰሜን ሜጫ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀበሉ።