
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቅድመ መከላከል ሥራ በቂ አለመሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በነዋሪውም ሆነ በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሚታየው ቸልተኝነት ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል የአብመድ የጋዘጤኞች ቡድን ታዝቧል፡፡
በተለይም ወረዳው የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው አዲስ አባባ እና ሞጆ ከተሞች በቅርብ ርቀት መገኘቱ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ በየቀኑም ከእነዚህ አካባቢዎች ወደ ወረዳው የሰው እና የተሽከርካሪ ፍሰት አለ፡፡ የአብመድ የጋዜጠኞች ቡድን ባደረገው ቅኝት ደግሞ በመግቢያ በሮች የሰውነት ሙቀት ልየታ እና ክትትል የማይደረግባቸው ቀናት አሉ፡፡ በመናኽሪያዎች፣ በካፍቴሪያዎች እና በገበያ ቦታዎችም የሚደረገው ጥንቃቄ አነስተኛ ነው፡፡
በአረርቲ ከተማ ሻይ በመሸጥ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ውባየሁ ዓድማሱ የጋዜጠኞችን ትዝብት ተጋርተዋል፡፡ “ሕዝቡ ዘንድ ምንም መደናገጥ የለም፤ ሁሉን ነገር በፈጣሪ ተስፋ በማድረግ ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክረ ሐሳብ እንኳን ያለመቀበል ችግር አለ” ብለዋል፡፡
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አቦሰጠኝ ባሕሩ ደግሞ “ኮሮና ከምደረ ገጽ እንደጠፋ አድርጎ የመመልከት ችግር አለብን” ሲሉ ስለበዛው መዘናጋት ተናግረዋል፡፡ በዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ አስደንጋጭ ዜና ቢነገርም የጤና ባለሙያዎችን እና የሃይማኖት አባቶች የሚያስተላልፉትን ምክር እየተገበሩ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት፡፡
አቶ አቦሰጠኝ እንዳሉት “በሌሎች ሀገራት ቅድሚያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከስቶ ብዙ ሕዝብን ለሞት መዳረጉ ትምህርት ሊሆነን ሲገባ በከተማ እና በዙሪያ ቀበሌዎች የበዛ ቸለተኝነት ታይቷል፡፡ ይህ ደግሞ ራስ ላይ እንደመፍረድ ስለሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ‘አህያዬን አስራለሁ፤ በፈጣሪም አምናለሁ’” የሚለው አባባል መተግበር አለበት ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ጎሳ ተስፋዬ ወረዳው ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጋላጭ ተብለው ከተለዩ ቦታዎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ምክትል ኃላፊው ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ኅብረተሰቡ የተቀመጡትን ምክረ ሐሳቦች የመተግበር ዝንባሌው ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም በሂደት መቀዛቀዝ ታይቷል፤ ሕግ ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ላይም የሥራ ኃላፊዎች ሽግሽግ በመካሄዱ ተፅዕኖ ፈጥሮ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ይህንን በማወቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እና የባሕሪ ለውጥ ማምጣት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ካሳሁን ሀብቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስከበር ሂደቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መተግበር እንዳለበት ከአዲስ እና ነባር የሥራ መሪዎች ጋር በመወያዬት ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ አራት ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ የሰውነት ሙቀት ልኬታው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ግብዓት መሟላቱንም ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ከፀጥታ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ከግንዘቤ ማስጨበጥ ሥራው ባሻገር ሕግ የማስከበር ተግባሩ በስፋት እንዲከወን ቁርጠኛ ውሳኔ መተላለፉንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡