የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ለተገኘው ሰላም ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ተገለጸ።

14

ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ውስጥ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሚና እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከኮሙኒኬሽን፣ ከሕዝብ ግንኙነት አመራሮች እና የሚዲያ አካላት ጋር የሚደረግ ክልላዊ ማጠቃለያ መድረክ በባሕር ዳር ተጀምሯል።

በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ያለፉት የለውጥ ሰባት ዓመታት በርካታ ስኬቶች እንደተመዘገቡባቸው ገልጸዋል። ፈተናዎችን በማለፍ ዘመን ተሻጋሪ ውጤቶች ለመመዝገባቸው የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉን ሚናም ጠቅሰዋል።

የሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ዘርፉ ኅብረተሰብን በአመለካከት ቀርጾ ወደ ተግባር በማስገባት እና ሀገርን በማሻገር በኩል የነበረው ሚና ከፍተኛ እንደኾነም ጠቅሰዋል። አማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት የገጠመውን ቀውስ ለመፍታት የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ለሕዝብ ትክክለኛውን መረጃ በማድረስ ሚናው ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያም ስኬቶችን እና ፈተናዎችን በመለየት ለቀጣይ ተግባራት ዝግጅት ለማድረግ ምክክር የሚደረግበት መኾኑን አንስተዋል። መድረኩን የከፈቱት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) በለውጡ ዓመታት የሕዝብ የዴሞክራሲ ጥያቄ መመለሱን አንስተዋል። በሀገር ውስጥም በውጪም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር ገብተው በሰላም እና በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ምኅዳሩ መስፋቱን ጠቅሰዋል።

የተቋማት ግንባታ ሥራም በልዩ ትኩረት መሠራቱን ጠቅሰዋል። ሁሉን የሚያስማማ ሀገራዊ ትርክት ለመፍጠርም እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ልማት፣ ሰላም እና መልካም አሥተዳደርን ለማሻሻል እና ለተግባራዊነቱ መሠራቱን አንስተዋል። በሰሜኑ ጦርነት ሀገሪቱ ተጋርጦባት የነበረውን አደጋ ሕዝብን በማስተባበር መቀልበሱ ሌላኛው ስኬት መኾኑን ዶክተር ዘሪሁን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ሲሠራ የቆየው አሉታዊ ትርክት ለጽንፈኝነት እንቅስቃሴ ምክንያት መኾኑንም አንስተዋል። ሰፋ ያለ የጽንፈኝነት እንቅስቃሴው በአማራ ክልልም በኢትዮጵያም ችግር ሲፈጥር መቆየቱን ተናግረዋል። በአማራ ክልልም ጽንፈኛ ኃይሎች ላለፉት ሁለት ዓመታት በምጣኔ ሃብታዊ እና በማኅበራዊው ዘርፍ በርካታ ጥፋት አድርሰዋል ብለዋል።

የጽንፈኛ ኃይሎች እንቅስቃሴ እንዲገታ እና ችግሩ ከመሠረቱም እንዲቋጭ ዘርፈ ብዙ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። ከክልሉ መንግሥት ጀምሮ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉም ሥራ በመሥራቱ አሁን ያለው የክልሉ አንጻራዊ ሰላም ተገኝቷል ብለዋል።

እስካሁን የሠራነው ሥራ እዚህ አድርሶናል ያሉት ዶክተር ዘሪሁን ነገር ግን ከሠራናቸው ይልቅ ያልሠራናቸው በርካታ በመኾናቸው በዚህ መድረክ ተመካክረን የቀጣይ ሥራዎችን አቅጣጫ እናስይዛለን ነው ያሉት።

በመጣንበት መንገድ የሚዲያ አካላት የነበራቸው ሚና እንዲሁም የቀጣይ አቅጣጫዎች ሚና ምን መኾን እንዳለበት እንወያያለን። አዲሱ የማኅበራዊ ሚዲያ ፈተና እያስከተለ ያለውን አሉታዊ የሕዝብ እንቅስቃሴ ለመከላከልም ቃኝተን እንሠራለን ብለዋል።

ዶክተር ዘሪሁን በውይይቱ መግባባት ላይ የሚደረስበትን አቅጣጫ ለሌሎችም በማስረጽ የሕዝብ ሰላም ለመጠበቅ መሥራት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“መንግሥት የመምህራንን ጥቅም እና ደኅንነት ለመጠበቅ እየሠራ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleሮቢንሁድ ራንሰምዌር