
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ”ትውልድ በመምህር ይቀረጻል፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ መልዕክት ክልላዊ የመምህራን ውይይት የማጠቃለያ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። ከሁሉም የክልሉ ዞኖች የተውጣጡ መምህራን በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ የፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ጉዳዮች፣ በትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት፣ በወቅታዊ የሰላም ችግሮች እና መፍትሔያቸው ላይ ተወያይተዋል።
ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መንግሥት አቅሙ በፈቀደ መጠን የመምህራንን የአካል እና የሙያ ደኅንነት ለማስከበር እንደሚሠራ ገልጸዋል። በተለይ በዚህ ዓመት የምጣኔ ሀብት እና ማኅበራዊ ልማቶችን ለመሥራት አቅደን ወደ ሥራ ገብተናል ብለዋል።
መምህራንን ማገት እና ማጎሳቆል እንደ ዝና የሚነገርበት የጸጥታ ችግር ውስጥ ነው ያለነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ መምህራን ማስተማር በሚችሉበት ኹኔታ ብቻ እንዲያስተምሩ፤ ችግር ባለበት ግን እንዳይጎዱ ጥንቃቄ እንዲደረግ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል። የወጡ ሕጎች የተፈጻሚነት ወሰን ቢኖራቸውም ለመምህራን የቤት መሥሪያ የቦታ ካሣ 318 ሚሊዮን ብር ለወረዳዎች መሰጠቱን ተናግረዋል።
እንደ ደረጃ ዕድገት እና መሰል የመምህራን ጥቅማ ጥቅሞች በሂደት በውይይት እንደሚስተካከሉም ጠቅሰዋል። መንግሥት ለትምህርት ጥራት እና ዕድገት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን የጠቀሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ነገር ግን አብዛኛውን በጀት ደመወዝ እንደሚወስደው እና ለትምህርት ኢንቨስትመንቱም የበለጠ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ተናግረዋል። በተለይም በሰው ኀይል ልማቱ ላይ መሠራት እንዳለበት አንስተዋል።
የክረምት ትምህርትን ጨምሮ የመምህራን ልማት ላይ ትምህርት ቢሮው በሚያቀርበው ሀሳብ መሠረት እንደሚወሰንም ገልጸዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ እየተተገበረ ያለው ሥርዓተ ትምህርት የአማራ ክልል ምሁራን የተሳተፉበት ስለኾነ በይኾናል አስተሳሰብ እና በግምት መንቀፍ ተገቢ አለመኾኑን አመላክተዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ የኢትዮጵያ ምሁራን በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ስምምነት እንደሌላቸው ጠቅሰው በታሪክ ብያኔ እና በትርክት ጉዳይ ላይ በደንብ መወያየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የጄአይጂ ክፍያን በተመለከተም በአማራ ክልል የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወሰነውን መፈጸሙን አንስተው ከመምህራንም አኳያ የክልሉ መንግሥት ያስቀረው ጥቅማጥቅም እንደሌለ ነው ያረጋገጡት።
በሰሜኑ ጦርነት የተሰው መምህራንን ቤተሰቦች ለመደገፍ የተረጋገጠ መረጃ እንዲቀርብ አሳስበው የክልሉ መንግሥትም የወሰነውን የድጋፍ መጠን ተጠቅመን እንሠራለን ብለዋል። የሚታየውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ችግር ለመግራት በሚያስቸግር የፖለቲካ አቋም እና የትግል ስልት የተፈጠረ መኾኑን አብራርተዋል። ስህተትን ስህተት ብሎ ዕውነቱን ከመጋፈጥ ይልቅ ተለሳላሽ የአመራር ባሕሪም የተደናገረ ሕዝብ መፍጠሩን አንስተዋል።
በአማራ ክልል ለተፈጠረው ግጭት መፍትሄ በመሻትም የአማራ ክልል መንግሥትም ኾነ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሰላም ጥሪ በይፋ ማቅረባቸውን አስታውሰው ከግጭቱ መከሰት በፊትም በሰላም እና በውይይት ለመፍታት በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን አንስተዋል። መንግሥት በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ በየትኛውም ርዕሰ ጉዳይ በሰላም ለመወያየት ጥሪ ማድረጉን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ታጣቂው ኀይል ግን የሰላም ጥሪውን ማጣጣሉን ገልጸዋል።
መምህራንም የክልሉን ችግር ምንጭ እና መፍትሄውን አስተውለው ለመፍትሄው መሥራት እና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው አሳስበዋል። አውሮፓውያን የነበረባቸውን የሃይማኖት እና የታሪክ ልዩነት ተወያይተው ወደ ምጣኔ ሀብት አንድነት እና አሁን ላይ ሁለገብ ወደኾነ አንድነት መምጣታቸውን በአብነት የጠቀሱት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
ለሕገ መንግሥቱ መሻሻልም ሕዝቦች ተወያይተው ሲግባቡ እንዲኹም የተዛባ ትርክትም በጦርነት ሳይኾን ተከባብሮ እና ተወያይቶ የሚስተካከል መኾኑን አንስተዋል። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም መንግሥት ከደመወዝ ጭማሪ ይልቅ የገንዘብ ዝውውር መቀነስን እና ሌሎችም ርምጃዎችን እየወሰደ መኾኑን አንስተዋል። ማዳበሪያ እና ነዳጅ እየተደጎመ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ መንግሥት በአንድ በኩል ሰላምን ለማስፈን ሁሉንም አማራጮች እየተገበረ በሌላ በኩል ልማት እንዳይቆም እና ዜጎች የበለጠ እንዳይጎዱ እየሠራ መኾኑን አመላክተዋል። ለሰላሙም ኾነ ለልማቱ መምህራን እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ከልብ መሥራት እና ሰላምን እና ልማትን መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው ነው ያሳሰቡት።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን