የአማራ ሕዝብ ትልቁ ጠላት ድህነት እና ኋላቀርነት ነው” ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)

14

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ለሁለንተናዊ ብልጽግና የነጋዴው ማኅበረሰብ ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ክልል አቀፍ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር)፣ የገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት መሐመድን ጨምሮ ሌሎችም የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር) የንግዱ ማኅበረሰብ በሀገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል። አምራች ዘርፉ የጎላ ሚና እንዲጫዎት በማድረግ ረገድ መንግሥት ሰፋፊ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ውይይቱ ባለፉት ዓመታት ያሳለፍነውን ውጣ ውረድ፣ የተገኙትን ስኬቶች እና ያጋጠሙ ፈተናዎችን ለይቶ መሥራት ነው ብለዋል። በንግዱ ማኅበረሰብ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን እና መፈታት የሚገባቸውን ጉዳዮች በተገቢው መንገድ በመገንዘብ በቀጣይ የእቅዳችን አካል አድርጎ ለመቀጠል ታስቦ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ እንደኾነ ነው የገለጹት።

ለንግድ እንቅስቃሴም ይሁን ለአጠቃላይ ልማት የሰላምን አስፈላጊነት አንድ ዓይነት ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል ያሉት ቢሮ ኀላፊው አሁን ያጋጠመን ጽንፈኝነት ህልሞቻችንን የማያሳካ፣ ልማታችንን የሚያደናቅፍ እና የልጆቻችንን ተስፋ የሚቀማ በመኾኑ የንግዱ ማኅበረሰብ አንድ ዓይነት አቋም በመያዝ በቃ ሊለው ይገባል ብለዋል።

ሰላም ከተረጋገጠ ልማት ይቀጥላል፣ የልማቱ ዋና ተዋናይ የኾነው የንግዱ ማኅበረሰብ ተረጋግቶ እና ከመንግሥት ጋር ተሳስሮ እንዳይፈጽም እንቅፋት የሚፈጥሩ የጽንፈኝነት አመለካከቶችን በአንድነት መታገል ይገባል ብለዋል። በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ነጋዴው ተንቀሳቅሶ እንዳይሠራ እያደረጉት ይገኛሉ፤ ይህንን የተዛባ አመለካከት እና የጥፋት መንገድ ተጽዕኖ የሚፈጥሩት በሕዝቡ ላይ በመኾኑ በአንድነት ልንታገለው ይገባል ብለዋል።

ነጋዴው ጠንካራ እንዲኾን፣ የመንግሥት እና የንግድ ማኅበረሰቡን መስተጋብር ለማጠናከር የዘርፍና የማኅበራትን አደረጃጀት ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል። የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ዘመናዊ አሠራርን ማዘመን ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ አካሄዶችን ከሌሎች ተቋማት ጋር በመኾን ለመፍታት በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት በክልላችን ባጋጠሙ ችግሮች የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የፖለቲካ ሥራዎቻችንን በአግባቡ እንዳንሠራ እንቅፋት ኾኖናል ብለዋል።

የንግዱ ማኅበረሰብ በነፃነት ተዘዋውሮ ለመነገድ፣ ገበሬው አምርቶ ወደ ገበያ ለማምጣት ፈተናዎች የነበሩ መኾኑን አስታውሰው አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም በመፈጠሩ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እና በንግዱ ማኅበረሰብ በኩል የፍጆታ ሸቀጦችን ለኅብረተሰቡ ለማድረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ መሻሻል እያሳየ መኾኑን ተናግረዋል።

ይህንን ተስፋ ዘላቂ ለማድረግ ሁሉም ማኅበረሰብ በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ ጥያቄ በመሳሪያ አይፈታም ያሉት ዶክተር ድረስ የአማራ ሕዝብ ትልቁ ጠላት ድህነትና ኋላቀርነት ነው ሲሉ ገልጸዋል። በውይይት የማይስተካከል የአሠራር ሥርዓት የለም፤ የንግዱ ማኅበረሰብም በጽንፈኝነት የተሰለፉ ወንድሞቻችንን በመምከር ወደ ሰላም እንዲመጡ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ክልሉ በችግር ላይም ኾኖ በርካታ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እና እየተመረቁ መኾኑንም አመላክተዋል። በየደረጃው በሕዝቡ የሚጠየቁ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች የሚመለሱት ሰላም ሲኖር በመኾኑ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር ተባባሪ በመኾን ሰላሙን መጠበቅ ይገባል ብለዋል።

ሸማችን እና አምራችን ማገናኘት የንግዱ ማኅበረሰብ ሚና በመኾኑ ጤናማ የንግድ ሥርዓት ለመፍጠር ደግሞ ነጋዴው ጤናማ አስተሳሰብ እና አወንታዊ አመለካከት ሊኖረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ንግድ እንዲሳለጥ ሰላምን ማስፈን ያስፈልጋል፣ ሰላምን ለማምጣት ደግሞ የንግዱ ማኅበረሰብ ሚናው የጎላ ነው ሲሉ ነው የገለጹት።

ክልሉ አሁን የገጠመውን ችግር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በመፍታት የተረጋጋ፣ በኢኮኖሚ የበለጸገ ክልል ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የንግዱ ማኅበረሰብ ከመንግሥት ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“በጽንፈኝነት አስተሳሰብ የሕዝብ ጥያቄ አይመለስም” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next article“ባሕር ዳር በሥራ ላይ ነች” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ