“በጽንፈኝነት አስተሳሰብ የሕዝብ ጥያቄ አይመለስም” አቶ ይርጋ ሲሳይ

9

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር እና ከደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ ከተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በወቅታዊ የጸጥታ እና የልማት ሥራዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢኒስቲትዩት ፕሬዝዳንት እሱባለው መሰለ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በጫካ የሚገኘው ኃይል እየሄደበት ያለው መንገድ ስህተት ነው ብለዋል። መንግሥት በኃይል እንደማይቀርም ተናግረዋል። ጽንፈኝነት ለበጌምድር ሕዝብ ጉዳት አመጣ እንጂ ያመጣው መልካም ነገር የለም ነው ያሉት።

ጽንፈኝነት የልማት ጥያቄዎች እንዳይመለሱ፣ ችግር እንዲመጣ አደረገ እንጂ ያመጣው ጥቅም አለመኖሩንም ተናግረዋል። “በጽንፈኝነት አስተሳሰብ የሕዝብ ጥያቄ አይመለስም” ያሉት ኀላፊው በጽንፈኝነት አስተሳሰብ የሕዝብ ጥያቄ ይመለሳል ብላችሁ ካሰባችሁ ሞኝነት ነው ብለዋል።

የጽንፈኝነት አስተሳሰብ እና ጽንፈኛ ለአማራ ሕዝብ እንደማይጠቅም እና የሕዝብ ጠላት መኾኑን ገልጸዋል። ጽንፈኝነት ወሰን እና ድንበር የለውም ያሉት ኀላፊው ጽንፈኝነት ሕዝብን እና ራስን እየበላ እንደሚሄድም ተናግረዋል። ከዚህ በላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ እና በእያንዳንዱ ቤት እንዳይገባ ጽንፈኝነትን መታገል ይገባል ብለዋል።

በንጹሐን ላይ በደል እና ችግር የሚያደርሱ ኃይሎችን ማውገዝ እንደሚገባ ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶች ስለ ሀገር እና ስለ ሕዝብ ሲሉ እውነትን እንዲሰብኩም ጠይቀዋል። የደም ነጋዴዎችን መለየት እና ማውገዝ ይገባል ነው ያሉት። የደም ነጋዴዎችን እየለየን ለሕዝብ ጥቅም እና ለሀገር አንድነት እንሠራለንም ብለዋል። ሀገራችሁን የምትወዱ ከኾነ ሀገርን የሚከፋፍል እና ለጠላት አሳልፎ የሚሰጥን ሃሳብ እና ድርጊት ማውገዝ አለባችሁ ነው ያሉት።

በጫካ የሚገኙ ኃይሎችን መክረው እና አሳምነው የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። መንግሥት ለሰላም የሚገቡትን እንደሚቀበልም ተናግረዋል።

ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ኾነው አካባቢዎችን እንዲጠብቁም አሳስበዋል። የአካባቢያችሁን ሰላም ካስጠበቃችሁ እውነትም የጀግኖች ልጆች ጀግኖች ናችሁ ብለዋል። የቀደመውን ታሪክ እየጠበቁ አዲስ ታሪክ እንዲሠሩም አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleክልል አቀፍ ፈተናዎችን በጊዜያቸው ለማስፈተን በቂ ዝግጅት ማድረጉን ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
Next articleየአማራ ሕዝብ ትልቁ ጠላት ድህነት እና ኋላቀርነት ነው” ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)