
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የስድስተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መከናወናቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል። ሱራፌል አየነው በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው ሸምብጥ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነው።
መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት ሰጥተውናል የሚለው ተማሪ ሱራፌል በአሁኑ ወቅት የዓመቱን የትምህርት ይዘት ከመሸፈን ባለፈ ልዩ ልዩ የመልመጃ ጥያቄዎችንም እየሠሩልን ይገኛሉ ብሏል። እርሱም በፕሮግራም እንደሚያጠና እና ወላጆቹም እንደሚደግፉት ተናግሯል። ጥሩ ዝግጅት በማድረጌ የተሻለ ውጤት እንደማመጣ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ ነው ያለው።
ተማሪ መክሊት አሸናፊ በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ስትኾን ጊዜዋን በፕሮግራም ከፋፍላ በማጥናት ለፈተናው ጥሩ ዝግጅት ማድረጓን ለአሚኮ ተናግራለች። ቤተ መጽሐፍት ሁሌ ክፍት ነው፤ የማካካሻ ትምህርትም ተሰጥቶናል፤ አሁን ላይ ያልተሸፈነ የትምህርት ዓይነት የለም ነው ያለችው። ተማሪ መክሊት ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንደተዘጋጀች ነው የተናገረችው።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ደመላሽ ታደሠ በዞኑ ለስድስተኛ እና ለስምንተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርት ተሰጥቷል ብለዋል። የየትምህርት ቤቶቹ ቤተ መጽሐፍት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ክፍት በማድረግ ተማሪዎች እንዲጠቀሙ መደረጉን ነው የተናገሩት።
በዞኑ የስድስተኛ ክፍል ፈተና በ15 ወረዳዎች እና በ58 ትምህርት ቤቶች ይሰጣል ብለዋል። 3 ሺህ 281 ተማሪዎችም ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት አቶ ደመላሽ። ክልላዊ የስምንተኛ ክፍል ፈተናው በ15 ወረዳዎች እና በ50 ትምህርት ቤቶች እንደሚሰጥም ተናግረዋል። 3 ሺህ 307 ተማሪዎችም ፈተናውን ይወስዳሉ ነው ያሉት።
ፈተናው በሰላም ተጀምሮ በስኬት እንዲጠናቀቅም የጸጥታው ሁኔታ ላይ የሚሠራ ግብረ ኃይልን በማወያየት ወደ ሥራ መገባቱን ነው አቶ ደመላሽ የተናገሩት። በደቡብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ የፈተና ባለሙያ የኾኑት ኤልሳቤጥ መላኩ የስድስተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በ13 ወረዳዎች ይሰጣል ብለዋል። አንድ ወረዳ ግን በጸጥታ ችግር የተነሳ አያስፈትንም ነው ያሉት።
ስድስተኛ ክፍል ላይ 140 ትምህርት ቤቶች 6 ሺህ 517 ተማሪዎችን የሚያስፈትኑ ሲኾን የስምንተኛ ክፍልን በተመለከተ ደግሞ 116 ትምህርት ቤቶች 7 ሺህ 893 ተማሪዎችን እንደሚያስፈትኑ ነው የተናገሩት። በሁለቱም የክፍል ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎች የማካካሻ፣ ማጠናከሪያ እና የሙሉ ቀን የቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ነው ባለሙያዋ የጠቆሙት። ፈተናው በሰላም እንዲሰጥም የፈተና ግብረ ኃይል ተሰይሟል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በተለይ ክልላዊ እና ሀገራዊ ተፈታኞች ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በትጋት እየሠራ መኾኑን ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ኢየሩስ መንግሥቱ ተናግረዋል። የቢሮው ዓላማ ተማሪዎችን ከማሳለፍ በላይ ነው ያሉት ወይዘሮ ኢየሩስ በየዓመቱ ከፈተና ውጤቶች የሚገኘው ግብረ መልስ የትምህርት ሥርዓቱን የወደፊት አቅጣጫም ያመላክታሉ፤ በዚህም መንግሥት ተጨማሪ የመፍትሄ ሐሳቦችን እንዲያዘጋጅ ይረዳዋል ነው ያሉት።
በ2017 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተናን 154 ሺህ 261 ተማሪዎች እንደሚወስዱ ነው ምክትል ኀላፊዋ የተናገሩት። ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡም በወላጆች እና በሌሎች ባለድርሻዎች ዘንድ ቁጭት የሚፈጥር ተወያይቶ የመግባባት ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል።
የትምህርት የሥራ ውጤት በሂደት የሚመጣ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ምክንያት የተሸራረፈው የትምህርት ክፍለ ጊዜን ለማካካስ ተሠርቷል ነው ያሉት።
2 ሺህ 822 የስድተኛ ክፍል ትምህርት ቤቶች የማጠናከሪያ ትምህርት ተሰጥቷቸዋል። በ2 ሺህ 167 የስምንተኛ ክፍል ትምህርት ቤቶች የማጠናከሪያ ትምህርት ተደራሽ መደረጉንም ወይዘሮ ኢየሩስ ተናግረዋል።
የየትምህርት ዓይነቶችን ይዘቶች የማጠናቀቅ ሥራም ተከናውኗል ነው ያሉት። ሁኔታዎች በሚፈቅዱባቸው አካባቢዎች ቤተ መጽሐፍት ከሰኞ እስከ ሰኞ ክፍት ተደርጓል ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ በ30 የስምንተኛ እና በ24 የስድስተኛ ክፍል ትምህርት ቤቶች የአዳር ጥናትም እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።
ለስድስተኛ፣ ስምንተኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሥነ ልቦና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም ቢሮ ኀላፊዋ ገልጸዋል። ካለፉት ዓመታት አንጻርም ዘንድሮ ጥሩ ዝግጅት በመደረጉ የተሻለ ውጤት ይጠበቃል ነው ያሉት።
የ2017 የትምህርት ዘመን የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከሰኔ 3 እስከ ሰኔ 4 /2017 ዓ.ም ድረስ ይሰጣል ብለዋል። የስድስተኛ ክፍል ፈተና ደግሞ ከሰኔ 5 እስከ ሰኔ 6 /2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን