ሴቶች በሌማት ትሩፋት ተጠቃሚ እየኾኑ ነው።

21

ጎንደር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በጎንደር ከተማ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሲዎስዱ የቆዩ ሴት አመራሮች በከተማው እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።

‎ሠልጣኞች በሴቶች የተሠሩ ሥራዎችን እና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ተግባራትን ነው የጎበኙት። በዚህም የዶሮ ርባታ፣ የወተት ልማት፣ የንብ ማነብ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ተጎብኝተዋል።

‎የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ሴቶች በሌማት ትሩፋት እና በከተማ ግብርና እንዲሳተፉ ከግብርና እና ከእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

‎ሴቶች እድል ከተሰጣቸው መሥራት እንደሚችሉ አሳይቷል ያሉት ኀላፊዋ ሴቶቹ የኢኮኖሚ ገቢያቸው እንዲጠናከር በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑ አንስተዋል።

‎ሴት የሥራ ኀላፊዎች የመጎብኘታቸው ምክንያት በቀውስ ጊዜም ኾኖ እየተሠሩ ያሉ ተግባራት በመልካም ተሞክሮ የሚወሰዱ በመኾናቸው በአካባቢያቸው እንዲደግሙት ያለመ ነው ብለዋል።

‎በሌማት ትሩፋት የተሰማሩ ሴቶች ከብዙ ፈተና ወጥተው በመልካም ሥራ ተሰማርተዋል ነው ያሉት። ‎ሴቶች የተሻለ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

‎በጉብኝቱ ያገኘናቸው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ ተመርጣ መብራቱ እና የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ አስችላ አማረ መልካም ተሞክሮዎችን ስለማግኘታቸው ተናግረዋል። በተለይም በጎንደር ከተማ የተጀመረውን የኮሪደር ልማት በአካባቢያቸው የገጠር ኮሪደር ለመድገም ቁርጠኛ ስለመኾናቸው ተናግረዋል።

‎በሚሠሩበት አካባቢ በቂ የእንስሳት ሀብት ዘርፍ መኖሩን ያነሱት የሥራ ኀላፊዎቹ ከጉብኝቱ ያገኙትን ተሞክሮ በመቀመር የተሻለ ተግባር ለመሥራት ስለማለማቸውም አንስተዋል።

‎ዘጋቢ፦ አዲስ ዓለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየዒድ አል አድሃ በዓል ሲከበር ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ታሳቢ ያደረገ መኾን እንደሚገባው የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ።
Next articleክልል አቀፍ ፈተናዎችን በጊዜያቸው ለማስፈተን በቂ ዝግጅት ማድረጉን ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።