
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ጀውሐር ሙሐመድ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ለሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 446ኛው የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል። የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በአደባባይ የሚከበር በዓል መኾኑን የተናገሩት ሼህ ጀውሐር በዓሉ ያለልዩነት በሰላም እና በደስታ ይከበራል ነው ያሉት።
በዒድ ወቅት የሚደረግ የእርድ ሥጋ ለሦስት ይከፈላል ያሉት ሼህ ጀውሐር አንድ ሦስተኛው ለምስኪን፣ አንድ ሦስተኛው ለጎረቤት ቀሪው አንድ ሦስተኛው ደግሞ ለቤተሰብ ማስተናጋጂያ ይውላል፤ ቆዳውም ለምስኪኖች ይሰጣል እንጅ አይሸጥም ብለዋል። የዒድ በዓል በሰላም፣ በአብሮነት እና በፍቅር ተከብሮ እንዲውልም ሁሉም ማኀበረሰብ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ሼህ ጀውሐር ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የትምህርት እና የደዓዋ ዘርፍ ኀላፊ መምህር ሼህ መሐመድ ኢብራሂም ለሙስሊም ማኀበረሰቡ እንኳን ለ1 ሺህ 446ኛው የዒድ አል አድሃ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ነው ያሉት። “ዒድ ማለት የደስታ ቀን ነው፤ ሰዎች ሰላማቸውን፣ አንድነታቸውን እና አብሮነታቸውን ነጭ ለብሰው በአደባባይ ሰላምን የሚያንጸባሩቁበት ነው” ብለዋል።
በዓሉ የጾታ እና የዕድሜ ልዩነት ሳይደረግበት ይከበራልም ብለዋል። የሙስሊሙ ማኀበረሰብ የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን ሲያከብር ወላጅ አልባ ሕጻናትን እንደ ልጆቹ እንዲቦርቁ፣ የተፈናቀሉ ወገኖች ተከፍተው እንዳይውሉ፣ ሌሎችንም ምስኪን ወገኖቹ ተደስተው እንዲውሉ ማድረግ ይገባዋል ነው ያሉት።
የፊታች አርብ የሚከበረው የዒድ በዓል በተለይ በባሕር ዳር ከተማ በጋጃ መስክ አደባባይ ሥነ ሥርዓቱ እንደሚከናወን ነው ሼህ መሐመድ ኢብራሂም የተናገሩት።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን