
ባሕርዳር፡ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) ማዕድኑ መገኘቱ የተረጋገጠው የአማራ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ በተያዘው በጀት ዓመት ባካሄደው የማዕድን ጥናት ነው፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ ባሶ ሊበን፣ ጎዛምን እና ደብረ ኤልያስ ወረዳዎች ደግሞ የግራናይት ክምችት እንዳላቸው በጥናቱ የተረጋገጡ ወረዳዎች ናቸው፡፡
የኤጀንሲዉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ይታየዉ ተስፋሁን ለአብመድ እንደተናገሩት በባሶ ሊበን እና ጎዛምን ወረዳዎች 67 ነጥብ 02 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የማዕድን ፍለጋና ክምችት ጥናት ተካሂዷል፡፡ በጥናቱም 21 ሚሊዮን 151 ሺህ 195 ነጥብ 2 ቶን በተለይ ለምንጣፍ የሚሆን የግራናት ማዕድን እንዳለ መረጋገጡንም አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይ በደብረ ኤሊያስ ወረዳ 28 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍና ጥናት ተካሂዶ 2 ሚሊዮን 438 ሺህ 100 ቶን የግራናይት ማዕድን መገኘቱን ነው ያብራሩት፡፡
የአማራ ክልል እምቅ የከበሩ ማዕድናት ባለቤት መሆኑን ያስታወቀው ኤጀንሲው ሀብቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም አመላክቷል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ1 ሺህ 775 ግለሰቦች የማዕድን ማምረት እና ምርመራ ፈቃድ እንደተሰጠም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውስጥም ስምንቱ በከፍተኛ የግንባታ ማዕድናት ማምረት፣ አራቱ በአነስተኛ የኢንዱስትሪ ማዕድናት ማምረት፣ 58ቱ አነስተኛ የግንባታ ማዕድናት ማምረት ፈቃድ የወሰዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ መረጃ አምስቱ የምርመራ፣ 1 ሺህ 691 የባህላዊ ማዕድናት ማምረት ፈቃድ አንዲሁም ዘጠኙ የከበሩ ማዕድናት ዕደ ጥበብ (ላፒደሪ) ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
ከዚህ በፊት የማዕድን ፈቃድ ወስደው ጉድለት ባሳዩ 155 የማዕድን ማምረት ፈቃዶች ላይ ማስጠንቀቂያ እና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ በአራት ፈቃዶች ላይ ዕገዳ መጣሉም ታውቋል፡፡
ርምጃው የተወሰደው በገቡት ውል መሠረት ወደ ሥራ ያልገቡ፣ በውላቸው መሠረት ክፍያ የማይፈጽሙ፣ ተቋሙን ሳያሳውቁ ሥራ ባቆሙ ላይ እንደሆነም ተብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡