“መፍትሄው ሰላማዊ ትግል መኾን አለበት” የፖለቲካ ፓርቲዎች

30

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በባሕር ዳር ከተማ የውይይት መድረክ አካሂደዋል። ለተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት እና ባሕል ግንባታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ እንደኾነ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት በኮምቦልቻ የኢዜማ ፓርቲ ሊቀመንበር ይማም በላይ ኢዜማ ሰላማዊ ትግልን መርህ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው ብለዋል። ከሁሉም በፊት ሰላም ይቀድማል ያሉት አቶ ይማም ሰላም ከሌለ ሀገር አይኖርም ነው ያሉት።

አሁን ላይ ሕዝባችን በችግር ውስጥ ይገኛል፤ ለዚህም ሁላችንም ያገባናል ብለዋል። አንድ ፓርቲ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ግዴታው ሊኾን እንደሚገባም ነው የተናገሩት። መንግሥት በሆደ ሰፊነት ሰላማዊ ጥሪን ማስቀጠል አለበት ነው ያሉት።

ኢዜማ እሳት ማርከፍከፍ አይፈልግም፤ ለሰላም እየሠራን ነው ብለዋል። ሌላው በውይይቱ ላይ የተገኙት የአብን ምክትል ሊቀ መንበር መልካሙ ፀጋዬ አብን በክልሉ ያለውን የሰላም እጦት በሰላም እንዲፈታ ጥረቶችን እያደረገ ነው ብለዋል።

አባሎቻችን እና መሪዎቻችን ሰላማዊ ትግልን መርሕ ያደረጉ ናቸው ነው ያሉት። የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ሰላም አስፈላጊነት የመምከር እና የማስገንዘብ ሥራ ሊሠሩ እንደሚገባም አቶ መልካሙ ገልጸዋል።

ታጥቀው በጫካ የሚገኙ ወንድሞቻችን ለውይይት እና ለድርድር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ስናደርግ ቆይተናል ብለዋል። ዛሬም ውይይትን እና ድርድርን እንዲመርጡ ጥሪ እናደርጋለን ነው ያሉት። መንግሥትም ተደጋጋሚ ጥሪን ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
ሰላማዊ ትግል መፍትሄ መኾን አለበት ነው ያሉት አቶ መልካሙ።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ሊቀ መንበር እና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተስፋሁን ዓለምነህ ሀገር እንደ ሀገር ልትቀጥል የምትችለው በሰላም ነው ብለዋል። እንደ አለመታደል ኾኖ የፖለቲካ ባሕላችን
በታሪክም በግጭት የታጠረ እንደኾነ ነው የገለጹት።

ይህ ኋላቀር ባሕል መቅረት አለበት ነው ያሉት። የፖለቲካ ትግል ሰላማዊ ብቻ መኾን እንዳለበት ነው የገለጹት። የትኛውም ዓይነት የሐሃሳብ ልዩነት ይኑር፤ የምንፈታበት መንገድ በሰላም መኾን አለበት ነው ያሉት። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣንን የሚይዙት በሰላማዊ እና
በሕዝብ ምርጫ ብቻ መኾን እንዳለበት ተናግረዋል።

የነገን ተስፋ የምናስብ ሁሉ ዛሬን እየገደልን መኾን የለበትም ብለዋል። በበጫካ ያሉ ወንድሞቻችን የትግል ሜዳውን ጠረጴዛ ላይ ማድረግ እንዳለባቸው ነው የገለጹት። ሰላም ይቅደም። የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ላይ አተኩረን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ክልሉ ከገባበት ቀውስ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ መኾኑን በማመን ጥልቅ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

ከችግሩ ለመውጣትም ሚናችን ምን መኾን አለበት የሚለው ላይ እንደገመገሙ ነው የተናገሩት። ከፖለቲካ ባሕላችን አንጻር ከፓርቲዎች ጋር መወያየት እና መገምገም አስፈላጊ በመኾኑ ውይይቱ መሠረታዊ እንደነበር ነው የገለጹት።

በጫካ ያሉ ወንድሞች የሰላም አማራጮችን እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው። ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ዶክተር ዘሪሁን። ይህን ዕድል ሁሉም እንዲጠቀሙት በማድረግ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ መኾን አለበት ነው ያሉት።

በሁሉም አካባቢዎች ሕጋዊነት እንዲሰፋ ፓርቲዎች የተጠናከረ ሥራ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleተጨማሪ ጥፋት እንዳይመጣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን መስበክ አለባችሁ።
Next articleየዒድ አል አድሃ በዓል ሲከበር ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ታሳቢ ያደረገ መኾን እንደሚገባው የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ።