
ደብረታቦር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር፣ ከደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ ከተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በወቅታዊ የጸጥታ እና የልማት ሥራዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ ሰላም ካለ ሁሉም ነገር አለ ብለዋል። እናንተ የሰላም ቀንዲል ናችሁ ብለዋቸዋል። የክልሉ እና የሀገሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በሕዝብ እና በመንግሥት የጋራ ትግል እየተመለሱ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደ ሀገር ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የአማራ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄዎችን ሰንዶ ማቅረቡንም አንስተዋል። የአማራ ሕዝብ በራሱ ልጆች መሰቃየት እና መንገላታት እንደማይገባውም ገልጸዋል። ሕዝብን እያሰቃየ የሚገኘውን ጽንፈኛ ኀይል መታገል እንደሚገባም ተናግረዋል።
ጽንፈኛው ኀይል ለሽምግልና እና ለዕርቅ የሄዱ ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን አንገላቶ መግደሉን ነው የገለጹት። የልማት ሥራ እንዲመጣ ከተፈለገ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች ስለ ዕውነት መስበክ እና መናገር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች የሚያስመልሷቸው ሕዝብ እና መንግሥት ናቸው ያሉት ኀላፊው ጽንፈኛው ኀይል የአማራን ሕዝብ ጥያቄ የማስመለስ ዓላማም አቅምም የለውም ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች ነጻ ኾነው ስለ ዕውነት እንዲመሰክሩ እና ለዕውነት እንዲወግኑ ጠይቀዋል።
በጫካ የሚገኙ ኀይሎችን ለሰላም እንዲገቡ እንዲመክሩም አሳስበዋል። ሰላምን የመረጡ ጀግኖች ናቸው፣ ሌሎችም ይሄን አማራጭ እንዲከተሉ እንፈልጋለን ነው ያሉት። የአካባቢያቸውን ሰላም እና ደኅንነት በአንድነት እንዲጠብቁም አሳስበዋል።
መንግሥት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ እያቀረበ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው አማራጫቸውን ጠመንጃ ባደረጉት ኀይሎች ላይ ግን ሕግ እናስከብራለን ብለዋል። “ተጨማሪ ጥፋት እንዳይመጣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን መስበክ አለባችሁ” ነው ያሉት።
ሕግ እና ሥርዓት እያስከበረ ላለው የጸጥታ ኀይል ድጋፍ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል። የጸጥታ ኀይሉ መስዋዕት እየከፈ ለሰላም መስፈን እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ አማረ ሰጤ አሁን ላለው ችግር ያጋለጠን የእሴት መሸርሸር ነው ብለዋል።
አኹን ላይ ትልቅ የማይከበርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ያሉት ምክትል አፈጉባኤው የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች መዋረዳቸውን እና በግፍ መረሸናቸውን ገልጸዋል። ትውልድን የሚቀርጹ መምህራን መገደላቸውንም አንስተዋል። ከአማራ ሕዝብ እሴት፣ ባሕል እና ታሪክ ያፈነገጠ ተግባር የሚፈጽሙ ጽንፈኞችን መታገል እንደሚገባም ገልጸዋል።
ጽንፈኛው በየመንገዱ ንጹሐንን እያገተ ገንዘብ እንደሚቀበል እና ሕዝብ መደበኛ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ እያደረገ ነው ብለዋል። አማራን እያሰቃዩ ለአማራ እታገላለሁ ማለት ውሸት ነው ያሉት አፈጉባኤው ይሄን አካሄድ መታገል ይገባል ነው ያሉት።
የልማት ሥራዎችን የሚያስቆመውን ኀይል መገሰጽ እና መምከር ከሃይማኖት አባቶች እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ በማራቅ የሕዝብ ጥያቄ እንደማይመለስ ተናግረዋል። የሃይማኖት አባቶች ዕውነትን መስበክ እና ጥፋተኛውን መገሰጽ አለባችሁ ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ ፍትሐዊ ጥያቄዎች አሉት ያሉት ምክትል አፈጉባኤው የፍትሕ ጥያቄዎች የሚመለሱት ግን በሕግ እና በሥርዓት ነው ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች ግጭትን ሳይኾን ሰላምን መስበክ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ሕዝብ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች መንግሥት እንደሚመልስም ገልጸዋል።
የማዳበሪያ አቅርቦት በተሳለጠ መንገድ እንዲደርስ በየመንገዱ መኪና የሚያስቆሙትን እንዲታገሏቸው አሳስበዋል። የተጀመረውን ሰላም ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አስገንዝበዋል።
ለሰላም የገቡ ኀይሎች አሉ ያሉት ምክትል አፈጉባኤው የገቡት ብለሆች እና ጀግኖች ናቸው፣ ሌሎችም እንዲመጡ የበኩላችሁን ተወጡ ብለዋል። ሰላም ካለ መንግሥት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን እየፈታ ይሄዳል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን