
ሰቆጣ: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት እየመከረች ትገኛለች። ወጣቱ ትውልድም ከሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ራሱን በማራቅ ለሀገር ሰላም በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ተናግረዋል።በጦርነት የሚገኝ ጥቅም አለመኖሩን በመረዳት በጉልበት ነገሮችን ለመፍታት መሞከር እንደማይገባ ወጣት ቢንያም አለልኝ ገልጿል።
በሰሜኑ ጦርነት ያሳለፍነው ይበቃናል የሚለው ወጣቱ ልዩነቶችን እና ችግሮችን ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመምከር መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል። አባቶቻችን ለዘመናት በሰላም እና በፍቅር እንዲኹም በመቻቻል ያጸኗትን ሀገር እኛ ወጣቶች ልንጠብቃት ይገባል ያለው
ደግሞ ወጣት አረጋው ደባሽ ነው።
የዋግ ኽምራን ሰላም ለማጽናት ወጣቱ ከጸጥታው መዋቅር ጋር በቅንጅት እየሠራ መኾኑንም ነው የተናገረው። በተያዘው ዓመት ብቻ በዋግ ኽምራ ከ400 በላይ የታጠቁ ኀይሎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተሀድሶ ሥልጠና ወስደው ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እየኖሩ መኾኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታ ምክትል ኀላፊ ጌታወይ አብርሃ ተናግረዋል።
ምክትል ኀላፊው የውጭ ኀይሎችን ተልዕኮ ለመፈጸም ሀገር እንድትፈራርስ መሥራት እንደማይገባ ጠቁመዋል። በዋግ ኽምራ ያለውን ሰላም ለማጽናት የጸጥታ መዋቅሩ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከወጣቱ ጋር ተቀራርበው እየሠሩ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የታጠቁ ኀይሎች መንግሥት ያቀረበውን ያልተገደበ የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ማኅበረሰባቸው እንዲቀላቀሉ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ጌታወይ ችግሮች ካሉም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንዲመክሩ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን