ሴቶች የሰላም መሠረቶች፣ የልማትም ሁነኛ ተዋናዮች ናቸው።

14

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት “ሴት የሰላም አምባሳደሮችን ማደራጀት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት ከተለያዩ ማኅበራዊ መሠረቶች ወካይ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ከኾኑ ሴቶች ጋር በጎንደር ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር)፣ የሰላም ሚኒስቴር ግጭት አሥተዳደር መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ይርጋለም መንግሥቱ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢሌኒ ዓባይ እና ከተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች እየተሳተፉ ነው።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) ሴቶች የሰላም መሠረቶች፣ የልማትም ኹነኛ ተዋናዮች ናቸው ብለዋል። ሴቶች በሰላም እሴት ግንባታ ላይ የላቀ ተፈጥሯዊ ባሕሪ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲ የሴቶችን አቅም በመረዳት አደረጃጀት ፈጥሮ ተሳትፏቸውን እያሳደገ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። የፓርቲው የሴቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት እስከ ቀበሌዎች የሚደርስ መዋቅር አለው፤ በዚህ መዋቅር መሠረት ሴቶችን የማንቃት እና የማብቃት ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት። በዚሁ መዋቅር በተፈጠረው ግንዛቤም ሴቶች ውጤታማ የልማት እና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ውስጥ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ግጭት ተቀርፎ አኹን ለተገኘው ሰላም የሴቶች ሚና ከፍተኛ እንደነበርም አብራርተዋል። ሴቶች የሰላም አምባሳደሮች መኾናቸውን በውል በመረዳት ተጨማሪ ግንዛቤ ሊፈጥሩላቸው የሚችሉ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ስለመኾኑም አንስተዋል።

ሴቶች ሰላም በደፈረሰ ጊዜ ቀዳሚ ተጎጅዎች ናቸው፤ የተጎዱ ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችን በመደገፍ እና ሥነ ልቦናቸውን በመገንባት በኩል ጠንካራ ናቸው ነው ያሉት ዶክተር መሥፍን። ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ በማሳተፍ ጥንካሬያቸውንም በሚገባው ልክ ለሀገር ልማት እና ለሰላም ግንባታ ማዋል እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሰላም ሚኒስቴር የግጭት አሥተዳደር መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ይርጋለም መንግሥቱ በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ ግጭቶች በሰላም እንዲቋጩ ሴቶች የበኩላቸውን ሚና ሲወጡ መቆየታቸውን ጠቁመዋል። በተለይም እናቶች ወጣት ልጆቻቸውን በመምከር አጥፊ ከኾነው ግጭት አውጥተዋል፤ ወደ ሰላማዊ ኑሮም መልሰዋል ነው ያሉት።

ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው በሰላማዊ ንግግር እና በየአካባቢው በሚገኙ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች መኾኑንም ተናግረዋል። ሴቶች ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት የሚያስችሉ ስልቶች አሏቸው፤ የሰላም ሚኒስቴርም ሴቶች ለሰላም ግንባታ በሚሠሯቸው ሥራዎች ሁሉ በትብብር እየሠራ ነው ብለዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የራስን ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ አቶ ይርጋለም ተናግረዋል። በአማራ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ዘላቂ እልባት ለመስጠትም በክልሉ በሚገኙ አምስት ዋና ዋና ከተሞች ለሰላም ግንባታ የሚሠሩ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተቋቁመው እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢሌኒ ዓባይ ሴቶች በተለይም እናቶች ልጆቻቸውን በመምከር እና ወደ ሰላም በመመለስ አኹን ለተገኘው የክልሉ ሰላም የማይተካ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል። የሰላም ጠንቅ የኾኑ አስተሳሰቦችን የያዙ አካላትን በእናትነት ቀርቦ በመምከር ከክፉ ነገር እንዲመለሱ አድርገዋልም ብለዋል።

የክልሉን ሕዝብ ሰላም ለመጠበቅ ሌት ተቀን ለሚሠሩ የጸጥታ አካላት ድጋፍ በመስጠትም የሰላም ዘብነታቸውን አስመስክረዋል ነው ያሉት።”የትኛዋም እናት ሰላምን የሚያደፈርስ ሀሳብ አታዋጣም” ያሉት ኀላፈዋ እናቶች ለሰላም ያላቸውን በጎ ተጽዕኖ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ሀገር መጠቀም
ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል የሰላም አምባሳደር ከኾኑ ሴቶች ጋር የሚደረገው ውይይት በተለያዩ ከተሞች እንደሚካሄድ እና እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ ሴቶችን አሳታፊ እንደሚያደርግም ኀላፊዋ ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሰላም ናፍቆናል!
Next articleወጣቱ ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባው የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።