ሰላም ናፍቆናል!

17

ደብረታቦር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር እና ከደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ ከተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በወቅታዊ የጸጥታ እና የልማት ሥራዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በጌምድር የጀግና ምድር ነው፣ ለሀገር አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሕዝብ ነው፣ በተለያዩ ዘመናት ለሀገር መስዋዕትነት ከፍሏል ብለዋል። ተሳታፊዎቹ አኹን ላይ በውስጣችን በተፈጠሩ ኀይሎች ዋጋ እየከፈልን ነው፣ ስቀን እንዳናሠርግ፣ አልቅሰን እንዳንቀብር ኾነናል ነው ያሉት።

የጣት ቀለበት፣ የጀሮ ጌጥ ሳይቀር እየተቆረጠ እየተወሰደ መኾኑንም ገልጸዋል። ብዙዎች በየመንገዱ ተዘርፈዋል፣ ተገድለዋል፣ ሀብታቸውን ተነጥቀዋል፣ መከራው ጸንቷል ነው ያሉት። ችግር የሚፈታው በውይይት እና በምክክር ነው ያሉት ኀላፊዎች በጫካ የገቡ ኀይሎች ወደ ሰላም እንዲመለሱም ጠይቀዋል።

ነፍስ እና ስጋን የሚያስታርቁ የሃይማኖት አባቶች እየመከሩ መመለስ አለባቸው ነው ያሉት። በየጊዜው ገንዘብ እየከፈሉ፣ እየተደበደቡ እና እየተዳፉ መኖር መሮናል ብለዋል። በየመንገዱ ገንዘብ የሚቀበሉ እና የሚዘርፉ ወንበዴዎች መብዛታቸውንም ገልጸዋል።

ልጆቻችን መክረን ካልመለስን ወደ ከፋ ችግር መግባታችን አይቀርም ነው ያሉት። ልጆቻችን ወደ ሰላም መልሰን በሰላም መኖር አለብንም ብለዋል።በሰላም ችግር ምክንያት ማዳበሪያ በአግባቡ እየደረሰን አይደለም ነው ያሉት። ሰላም ናፍቆናል፣ ስለ ሰላም እንዘምር፣ ስለ ሰላም እንስበክ፣ በግጭት ያገኘነው ነገር የለም ነው ያሉት።

ትውልድ እየጨለመበት ሲመጣ ዝም ብለን ማየት ሞኝነት ነው ሲሉም ተናግረዋል። ሰው በትውልድ ቦታው ተሳቅቆ እየኖረ ነው፣ ሰላም እና ልማት ሊናፍቀን ይገባል ብለዋል። ሰላምን በማረጋገጥ ልጆቻችን እንዲማሩ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

ከመለያየት፣ ከመጠላላት መውጣት እንደሚገባም ነው የተናገሩት። ከክፉ ነገር ሽሽ፣ ሰላምን ፈልጋት፣ ተከተላትም እንደተባለ ሁሉ ሰላምን መፈለግ እና መከተል እንደሚገባ ተናግረዋል። ከሰላም ማጽናት ጎን ለጎን የልማት ሥራዎች እንደሚሠሩም ነው የተናገሩት።

የአየር መንገድ፣ የኢንቨስትመንት እና ሌሎች የልማት ሥራዎች እንዲሠሩላቸውም ጠይቀዋል። የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደበበ አክሎግ በከተማዋ ለሚነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች መልስ እየሰጡ እንደሚሄዱ ገልጸዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ሰላምን ካልፈለግነው ፈልጎን አይመጣም ነው ያሉት። በዚህ ወቅት ከሰላም የበለጠ አጀንዳ የለንም ብለዋል። የጥላቻ ሥራ አይጠቅመንም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የሚጠቅመን ፍቅር እና ይቅር ባይነት ነው ብለዋል። የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ እርስ በእርስ መጋጨት እንደማያስፈልግም ተናግረዋል።

አደገኛ የኾነውን የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ማረም እና ማስተካከል እንደሚገባም ገልጸዋል። ጽንፈኞችን ከጀግኖች ጋር ማቀላቀል እንደማይገባም ተናግረዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በዞኑ ለተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም አስተዋጽኦ አድርገዋልም ብለዋል።

ያለ እናንተ ድጋፍ እዚህ አልደረስንም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ለሰላም መጽናት የምታደርጉትን ድጋፍ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ እንፈልጋለን ነው ያሉት። የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የማዳበሪያ አቅርቦት በተሟላ መልኩ ለማድረስ እንደሚሠሩ የተናገሩት ዋና አሥተዳዳሪው የማዳበሪያ አቅርቦት እንዳይዘገይ በየመንገዱ የሚዘርፉ ኀይሎችን መታገል አለባችሁ ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢኒስቲትዩት ፕሬዝዳንት እሱባለው መሰለ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የመደመጥ አቅማቸው ትልቅ መኾኑን ገልጸዋል። ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በተደጋጋሚ መወያየት ደግሞ ከገጠመን የጸጥታ ችግር ለመውጣት ያስችላል ነው ያሉት።

ችግሮችን ለመፍታት ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር መግባባት እንደሚገባም ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ያላቸውን ተደማጭነት ተጠቅመው ለሰላም መስፈን ከልባቸው እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

በየቦታው ያለውን ጽንፈኛ ቡድን እየመከሩ እና እየገሰጹ ማምጣት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት መጀመሪያ የተረጋገጠ እና የተረጋጋ ሰላም መፍጠር አለብን ብለዋል። ዕውነት ላይ በመቆም ለዘላቂ ሰላም መስፈን መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

በሀሰተኛ መረጃ ያልተገባ ሀሳብ መያዝ እና ወደ አልተገባ መንገድ መሄድ እንደማይገባም አሳስበዋል። በጫካ የሚገኙ ወገኖችን በመምከር የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉም ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። ችግሮችን ለመጋፈጥ ዝግጁ በመኾን ለዘላቂ ሰላም መሥራት ይጠበቃልም ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article”ምን ችግር እንደገጠመን ቆም ብለን ማሰብ የሚገባን ጊዜ ላይ ነን” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next articleሴቶች የሰላም መሠረቶች፣ የልማትም ሁነኛ ተዋናዮች ናቸው።