”ምን ችግር እንደገጠመን ቆም ብለን ማሰብ የሚገባን ጊዜ ላይ ነን” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

10

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ”ትውልድ በመምህር ይቀረጻል፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ መልዕክት ክልላዊ የመምህራን ውይይት የማጠቃለያ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምሀርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የሀገራችን እና የክልላችን አሁናዊ ሁኔታን በመረዳት ከማን ምን እንደሚጠበቅ በመወያየት ሁሉም የየድርሻውን እንዲወጣ እና የአረዳድ ክፍተቶችንም በመሙላት የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ መድረኩ መዘጋጀቱን አንስተዋል።

ሀገር የሁላችን ናት፤ እናም ልማቷም ውድቀቷም የሁላችን ነው ብለዋል። ለዚህም በየተሰለፍንበት የሥራ መስክ በመሥራት የጋራ ብልጽግናን ዕውን ማድረግ አለብን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ቀደምት ነጻነት፣ ሥልጣኔ እና ዕድገት የነበራት ብትኾንም ዛሬ ላይ ምን ችግር እንደገጠመን ቆም ብለን ማሰብ የሚገባን ጊዜ ላይ ነን ብለዋል።

በዓለም ላይ የተለያዩ ግጭቶች አሉ፤ ልዩ የሚያደርገው ግን የምንፈታበት መንገድ ነው፤ ስለ ሀገራችን መጻዒ ዕጣ የምንወስንበት ጊዜ ላይ በመኾናችን በዚሁ ላይ ለመምከር ያደረጋችሁትን ጥረትን አደንቃለሁ ብለዋል።

ትምህርት የሁሉም ሙያ ምንጭ፤ መምህርም የሁሉም ምሁር አባት በመኾኑ ችግሮችን ለመፍታት ባለፉት የውይይት መድረኮች ለተደረገው ተሳትፎ እና አበርክቶም መምህራንን አመሥግነዋል።

ለልጆቻችን ጥሩ ሀገር ለማስረከብ ምን መሥራት እንዳለብን የሚያመላክቱት መምህራን በመኾናቸው ትውልድ እንዴት ይቀረጽ በሚለው ጉዳይ ላይ አጽንኦት ሰጥተው ሊመክሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleከተሞችን ለኑሮ ብቻ ሳይኾን ለምርት እና ምርታማነት ምቹ ለማድረግ መሥራት ይጠበቃል።
Next articleሰላም ናፍቆናል!