
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ”ትውልድ በመምህር ይቀረጻል፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ መልዕክት ክልላዊ የመምህራን ውይይት የማጠቃለያ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተከፍቷል። ውይይቱን ያስጀመሩት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ትምህርት ለሀገር ልማት ያለውን ሁነኛ መሣሪያነት አንስተዋል።
መምህራን ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ፣ እንዳያስተምሩ እና መምህር ነን ለማለት እስኪሰጉ ድረስ ሲደርስባቸው የከረመውን ስጋት፣ ወከባ፣ አፈና እና ግድያ አንስተዋል። የትምህርት ዋነኛ አቅም እና መሣሪያዎች መምህራን መኾናቸውን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ ዘመኑ በማኅበራዊ ሚዲያ እና በስሜት በሚነዳበት ወቅት የማስተካከያ ዋናው መሣሪያ ትምህርት እና ዕውቀት መኾኑን አንሰተዋል። ከዕውቀት እና ክህሎት በተጨማሪም ለሥነ ምግባር ቀረጻም ዋናው መሣሪያ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ትውልዱ የግብረ ገብነት ችግሮች እያጋጠሙት መኾኑን አንስተዋል። ይህንን ለማስተካከልም የትምህርት ቤቶች እና መምህራንን አስኳልነት ጠቅሰዋል። የዚህ በጎ እሴት አመንጭ መምህራን ላላቸው አስተዋጽኦ አመሥግነዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ በየደረጃው የተደረገ የመምህራን መድረክ እንደነበር አስታወሰው የዚህ መድረክ ዓላማም ሥርዓታዊ በኾኑ ችግሮች ላይ ለመምከር እና በጎ ልምዶችን ለመለዋወጥ መኾኑን አንስተዋል።
መንግሥት ሊከተለው በሚገባው አቅጣጫ ላይ ለመወያየት እና ለወደፊትም በአሳታፊ መልኩ ለመተግበር መኾኑንም ነው ያስገነዘቡት። በየደረጃው ውይይቶች የኅብረተሰቡን ሃሳብ ሰምተናል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ መምህራንም የኅብረተሰቡን ሃሳብ በማንሳት ውይይት እንዳደረጉ እና ጠቃሚ ሀገራዊ ሃሳብ እንዳነሱ መገንዘባቸውንም ገልጸዋል።
ክልሉ በትምህርት ዘርፍ የተለየ ስብራት አጋጥሞታል ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በርካታ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ማቋረጣቸውን ገልጸዋል። 60 በመቶ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀዋል፤ ሕይዎታቸውም አደጋ ተጋርጦበታል፤ ወጣቶች ለማኅበራዊ ጠንቅ ተጋልጠዋል ብለዋል። ዶክተር እና ፓይለት የመኾን ራዕይ የነበራቸው ሕጻናት የጦርነት ልምምድ ሲያደርጉ እንደሚስተዋሉ አንስተዋል።
ሌሎች ዘርፎች ላይ የሚያጋጥምን ችግር በቀጣዩ ዓመት ማስተካከል ቢቻልም ትምህርት ላይ የተደቀነው አደጋ ከፍተኛ እና ለማስተካከል አስቸጋሪ መኾኑን አንስተዋል። መምህራን ፖለቲከኞች፤ ትምህርት ቤቶችም የፖለቲካ መድረክ አይደሉም ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ትውልድን በሚቀርጹ እና ማኅበረሰብን በሚያገለግሉ መምህራን ላይ ጥቃት ሊፈጽምባቸው እንደማይገባም ተናግረዋል። ለሙያው ትልቅ ክብር ሰጥተው መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ መምህራን መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።
ተወያዮች በሀገር እና በክልል ደረጃ በትምህርት ሥርዓቱ እና በሰላም ጉዳዮች ላይ ጠቅላላ መምህራንን በመወከል ውይይት በማድረግ ለችግሮች የጋራ መፍትሄ ማበጀት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን