
ባሕርዳር፡ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) የዓባይ ጉዳይ ከዓለም አቀፋዊ ታላላቅ አጀንዳዎች አንዱ ሆኖ ይነሳል፡፡ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ድርድራቸውን የመጨረሻ ማሰሪያ አለማበጀት እና የአሜሪካና የዓለም ባንክ አድሏዊነት ጉዳዩን የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ ዓለም አቀፍ የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች መርሆዎች እና ተያያዥ ሐሳቦችን አንስተን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ጥናት መምህር እምቢአለ በየነ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ እንደ መምህሩ ማብራሪያ ተቀባይነታቸው እንደየ ሀገራቱ የተለያየ ቢሆንም የወሰን ተሻጋሪ ወንዞችን የሚመለከቱ ዓለም አቀፋዊ መርሆች አሉ፡፡
ቀደም ሲል የነበረው በተለይም አሜሪካ ወደ ሜክሲኮ የሚሄደውን ወሰን ተሻጋሪ ወንዟን የተጠቀመችበት ሂደት “ሃርሞን ዶክተሪን” የሚባለው መርህ ነው፡፡ ይህም ውኃው የሚነሳባቸው ሀገራት ማንንም ሳያማክሩ የፈለጉትን መጠቀም እንደሚችሉ ያመለክታል፤ ይህም ሉዓላዊ መብታቸው እንደሆነ የሚያሳይ መርህ ነበር፡፡ አሜሪካም ይህን መርህ በመጠቀም በወንዟ ላይ የፈለገችውን ስታደርግ ነበር፡፡ ሌላው “አብሶሊዩት ቴሪቴሪያል ኢንቴግሪቲ” ወይንም የግዛት አንድነት የሚባለው መርህ ነው፤ በዚህ መርህ መሠረት ወደታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት የሚሄድ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ፍሰት በፍጹም መነካት የለበትም የሚል እሳቤ አለ፤ ይህ መርሆ ግን ቅቡልነቱን ካጣ ቆይቷል፤ የሀርሞን ዶክትሪን ተቃራኒም ነው፡፡
በዚህ ወቅት ተቀባይነት ያለው መርህ ምክንያታዊና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚለው መርህ እንደሆነም ምሁሩ ተናግረዋል፡፡ ይህ መርህ ደግሞ በተፋሰሱ ሀገራት ጉልህ ጉዳት አለማድረስ የሚለውን በትኩረት የሚመለከት ነው፡፡
በአፍሪካ ከ60 በላይ በዓለም ላይ ደግሞ ከ260 በላይ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች እንዳሉ የገለጹት መምህሩ ከእነዚህ ወንዞች እንደዓባይ ዓይነት ባሕሪ ያላቸው፣ ውይይት የሚደረግባቸውና የታችኞቹ ሀገራት ‘‘እኔ ካልፈቀድኩ’’ የሚሉባቸው እንደሌሉም አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ምክንያታዊና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገውን መርህ ለረጅም ጊዜ መያዟንም ተናግረዋል፡፡ ግብጽ በአንጻሩ “የታችኞቹው ሀገራት ሳይፈቅዱ የላይኞቹ ሀገራት ምንም ማድረግ አይችሉም” የሚል መርህ የምታራምድ ናት፡፡ (እ.አ.አ) በ1966፣ በ1997 እና በ2004 በነበሩ ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ምክንያታዊና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚለው መርህ እንደተካተተም ምሁሩ አስታውሰዋል፡፡ ግብጽ እንደ መከራከሪያነት የምታነሳቸው (እ.አ.አ) የ1929 እና የ1959 ስምምነቶች ከመርሁ ጋር ግንኙነት የሌላቸው መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የግብጽ ውል እና ክርክር አንድም ጠብታ ከውኃው እንዳይነካ የሚል እንጂ ተቀባይት ያለውን መርህ ያከበረ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ የግብጽ ዓይነት አመለካከት ያለው ሀገር በሌሎች ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች በሚያገናኟቸው ሀገራት እንደሌምም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያስ ምን ታድርግ?
“የዓባይ ውኃ ከነዳጅ በላይ ነው” ያሉት ምሁሩ ዓባይ የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን ከታች እስከ ላይ ላለው ኢትዮጵያዊ ማሳወቅ ይገባል፤ ዓባይ የኅልውና ጉዳይ መሆኑንም ማስረዳት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር አንጻር የምግብ ፍላጎቷን ለማሟላትና የኃይል ተጠቃሚ ለመሆን ዓባይ ላይ መሥራት የግድ እንደሚላትም አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ለማሳካትም የዲፕሎማሲ ሥርዓቷን ማጠንከር ይጠበቅባታል፡፡
አሁን ላይ ግብጽ በዓባይ ጉዳይ የጠነከረችበትን ምክንያት ማጤን እንደሚገባም ምሁሩ ተናግረዋል፡፡ የሕዳሴው ግድብ ሲጀመር ምንም ያላለች ሀገር ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ “ያዙኝ ልቀቁኝ” የምትልበት ምክንያት የኢትዮጵያ ሁኔታ ስለተቀየረና የውስጥ ፖለቲካው ተበላሽቷል ብላ ስላሰበች እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም በቀላሉ በእጅ አዙር ነገሮችን ማበላሸት ወይም በግዴታ “እንድትፈርም እናደርጋታለን” ብለው በማሰብ እየሠሩ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ በመሆኑም ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ላይ መሥራት፣ የመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ማጠንከርና ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
“መንግሥት ይሄዳልም ይመጣልም፤ ሀገርና ሕዝብ ግን አይለወጥም” ያሉት ምሁሩ “ዓባይን ከስልጣን ጋር ማገናኘት የለብንም፤ ይህ ሀገራዊ ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓባይ ላይ መሥራት እንደሚገባቸውም መክረዋል፡፡
እንደ መምህሩ ማብራሪያ ተፅዕኖ አለ ከተባለ እንኳን ሊኖረው የሚችለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ነው፤ ለዚህ ደግሞ ለፀጥታው ምክር ቤት ተገቢ የሆነ ግንዛቤ መስጠት ከኢትዮጵያ ይጠበቃል፡፡ ግብጾች እያራመዱት ያለው ሐሳብ ስህተት መሆኑንና የቀኝ ገዥዎችን ሐሳብ “ተቀበሉ” እያሉ እንደሆነ ለምክር ቤቱን ማስረዳት ይገባልም ብለዋል፡፡ ሰላማዊ መንገዶችን ሁሉ አሟጦ መጠቀም እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡