
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ “የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት ክልላዊ የጤና ባለሙያዎች የውይይት መድረክ ተካሂዷል። የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አቡዱ ሁሴን (ዶ.ር) እንዳሉት አርበኝነት በተሠለፈበት የሥራ ዘርፍ ለማኅበረሰብ ተገቢውን አገልግሎት መሥጠት ነው።
የጤና ባለሙያዎች ባለፉት ዓመታት መስዋዕትነት እየከፈሉ በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ የማኅበረሰቡ ጤና የማስጠበቅ ሥራ መሥራታቸውን አንስተዋል። የጤና አገልግሎት ሙያ ብቻ ሳይኾን መንፈሳዊነትን ጭምር የተላበሰ ሙያ መኾኑን ያነሱት ምክትል ርዕሰ መሥተዳደሩ ባለሙያዎች መንፈሳዊነትን ተላብሰው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት መሥጠት ይገባል ብለዋል።
በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የመልካም አሥተዳደር፣ የመሠረተ ልማት እና የግብዓት ችግሮችን ለይቶ በወቅቱ መፍታት እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት። የሚነሱ ችግሮችን ሕግ እና ሥርዓትን በተከተለ መንገድ ማቅረብ ባሕል ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል። በቀጣይ በባለሙያዎች የሚነሱ ችግሮችን በመለየት በተቻለ መጠን ለመፍታት የሚሠራ ይኾናል ብለዋል።
የሚነሱ ችግሮች ደግሞ የግለሰብን ችግር ለመፍታት ሳይኾን የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል ካለው አስፈላጊነት አኳያ ታይቶ መኾኑን ገልጸዋል። በችግር ውስጥ ኾነው ሙያዊ ሥነ ምግባርን ተላብሰው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ለሠጡ ባለሙያዎችም ምስጋና አቅርበዋል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ባለፉት ዓመታት መከላከል እና አክሞ ማዳንን መሠረት ባደረገው የጤና ፖሊሲ ላይ በተሠራው ሥራ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል።
የጤና ባለሙያዎች ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በሰሜኑ ግጭት እና አኹን ላይም በክልሉ በተከሰተው ግጭት ችግር ሳይበግራቸው የማኅበረሰቡን ጤንነት የማሻሻል ሥራ መሥረታቸውን ገልጸዋል። የእናቶች እና ሕጻናት ሞት መቀነስ እና የተላላፊ በሽታዎች ሥርጭት መቀነስ ለአብነት ተጠቅሰዋል።
ኀላፊው እንዳሉት የመረጃ ሥርዓትን ለማዘመን የዲጅታል ጤና ሥርዓት የስድስት ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ ይገኛል። የግብዓት አቅርቦትን እና የሕክምናውን ዘርፍ ማሻሻል የሚያስችሉ ዘመናዊ እና ትላልቅ የሕክምና መሳሪያዎችን የማሟላት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ከፋይናንስ ጥገኝነት ለመላቀቅ የሀገር ውስጥ ሃብት እና የውስጥ ገቢ የማሰባሰብ ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
ተወዳዳሪ እና የተሟላ ሥነ ምግባርን የተላበሰ የሰው ኃይል ለመፍጠ እንደ ሀገር ጭምር እየተሠራ ይገኛል። የሥራ ባሕልን በማሻሻል የማኅበረሰቡን ጤና ማሻሻል ላይ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል። በቀጣይ በባለሙያዎች የተነሱ ጥያቄዎችን ከሌሎች የሙያ ማኅበራት ጋር በመኾን ለመፍታት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!