
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በባሕር ዳር ከተማ ውይይት እያደረጉ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲወቹ በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ፣ የፖለቲካ ፓርቲወች ተግባር እና ኀላፊነትን በተመለከተ እንዲሁም በዴሞክራሲያዊ ዕድገት ዙሪያ ነው ውይይት እያደረጉ ያሉት።
በውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከሰተው ቀውስ የሀገሪቱን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታውን አናግቶት ቆይቷል ብለዋል።
አሁን ላይ የነበረውን ቀውስ መጋፈጥ በመቻላችን እና ስለ እውነት በመታገላችን አንጻራዊ ሰላም ውስጥ እንገኛለን ነው ያሉት። ይህ እንዲመጣም ሁሉም በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው ሁሉ ጥረት በማድረጋቸው የመጣ ነው ብለዋል።
የክልሉ ሕዝብ እረፍት እንዲያገኝ፤ በሰላም አየር ውስጥ እንዲንቀሳቀስ እና አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ እንዲኾን የፖለቲካ ፓርቲወች ወሳኝ ሚና ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ከመጣንበት ክልላዊ ሁኔታ ብዙ መማር ይኖርብናል ብለዋል። በቀጣይ ክልሉን በዘላቂነት ለማሻገር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከልብ መምከር እና መዘከር አለብን ነው ያሉት።
ገዥው ፓርቲም ኾነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሁን ካለው የሰላም ሁኔታ አንጻር ትልቅ ተግባር ይጠበቅብናል ነው ያሉት። “ስለ ሀገራችን መፃዒ እጣ ፈንታ ፓርቲዎች መምከር እና መዝከር አለብን” ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን