
ደብረታቦር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር እና ከደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ ከተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በወቅታዊ የጸጥታ እና የልማት ሥራዎች ዙሪያ እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስቻለ አላምሬ፣ የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢኒስቲትዩት ፕሬዝዳንት እሱባለው መሰለ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ የሀገር ባለውለታዎችን ስላገኘን ደስታችን ከፍ ያለ ነው ብለዋል። በዞናችን ሁለት አይነት ሰዎች ይገኛሉ ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው አንዳንዶቹ ለሰዎች ሲሉ የሚሞቱ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ለጥቅም ሲሉ ሰው የሚገድሉ ናቸው ነው ያሉት።
በጋራ ሰላማችን አስጠብቀን ሀገራችን የጀመረችውን ልማት ማስቀጠል አለብንም ብለዋል። ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች መፍትሔ እንደማይጠፋም ተናግረዋል። ከአብራካችን የወጡ ነገር ግን በክፉ ተግባር የተሰማሩ ኀይሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴን በመገደብ እና ትምህርት በማቋረጥ አስከፊ በደል እያደረሱ ነው ብለዋል። ከዚህ አስከፊ ድርጊት በመውጣት ሰላምን ማረጋገጥ ይገባልም ነው ያሉት።
በተሠራው ሥራ ሰላም የብልሆች ምርጫ ነው ብለው የገቡ ኀይሎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ለሰላም ለገቡትም ምሥጋና አቅርበዋል። ሌሎችም እንዲመጡ ጠይቀዋል። ጽንፈኝነት አስነዋሪ ድርጊት የሚፈጸምበት አስተሳሰብ መኾኑንም ገልጸዋል። ጽንፈኝነትን አውግዞ የጋራ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም አመላክተዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኀይል በከፈለው መስዋዕትነት አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩንም ተናግረዋል።
ለራሳቸው ብለው ከሚገድሉን ራሳችንን በማራቅ ለሰው ብለው ራሳቸውን ለመስዋዕትነት ከሚያቀርቡ ጀግኖች ጋር በጋራ በመኾን ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በየጊዜው እያገኘን የምናወያያችሁ ኢትዮጵያ ሰላም ስለምትፈልግ ነው ብለዋል። የሃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ምክር እና ሚና እንደምትሻም ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ላቅ ያለ መኾኑንም አንስተዋል። በሰሜኑ ጦርነት የገጠመንን ችግር የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ባደረጉት አስተዋጽኦ በድል አልፈን ሀገራችን አስከብረናል ብለዋል። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕዝብን ለመከራ እና ስቃይ መዳረጉንም ገልጸዋል።
የክልሉ ሕዝብ መከራ እና ደስታን ለማሳለፍ ተቸግሮ ለሕዝቡ መሠራታዊ ፍላጎት ለማቅረብ ችግር ገጥሞት እንደነበር ነው ያነሱት። ውል የሌለው ግጭት ሕዝብን ለመከራ ዳርጓል ነው ያሉት። አሁን ላይ ብዙው ሰው ገብቶት የተሻለ ሰላም እና ብርሃን እያየን ነው ብለዋል። ችግሩን በደንብ በመገንዘብ ከችግሩ መውጣት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
“ጊዜው የሃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ምክር ይፈልጋል” ያሉት ኀላፊው መመካከር እና መወያየት ያስፈልጋል ብለዋል። ካለ እናንተ ድጋፍ እና ምክር የበጌምድር ችግር ሊቀረፍ አይችልም ነው ያሉት። እናንተ እያላችሁ ልጆች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ፣ የትውልድ ክፍተት እንዲኖር መፍቀድ የለባችሁም ብለዋል። ሰላም ከሌለ እና ትውልድ ከተቋረጠ ሀገር የሚረከብ ትውልድ እንደማይኖርም ገልጸዋል።
ከዚህ በላይ ችግር እንዳይፈጠር መምከር እና መወያየት እንደሚገባ ተናግረዋል። ሕዝቡ መከራ እንደሚበቃውም ገልጸዋል። ሕዝቡ ልማት፣ ሕጻናት ደግሞ ትምህርት ይፈልጋሉ ነገር ግን ይህ እየኾነ አይደለም፣ ትምህርት እና ልማት እንዳይኖር ያደረጉትን ማስቆም ይገባል ነው ያሉት። መንግሥት የሰላም በሩን ከፍቷል ያሉት ኀላፊው በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች ዕድሉን መጠቀም እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ለነገ ሀገር ተረካቢ የኾኑ ወጣቶችን እንዳናጣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የድርሻችሁን ልትወጡ ይገባል ነው ያሉት። ችግሩን በዚህ ወቅት ካልቋጨነው ራሳችን ለጠላቶቻችን አሳልፈን እንሰጣለን ብለዋል። ይህ እንዳይኾን የውስጥ አንድነትን ማጠናከር እና ችግርን መፍታት ይገባል ብለዋል።
የበጌምድር ሕዝብ ጀግና፣ ለሀገር መስዋዕትነት የሚከፍል ነው ያሉት ኀላፊው ነገር ግን በየጊዜው በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ሕዝቡ መጠቀም የሚገባውን አልተጠቀመም ነው ያሉት። ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲኾን ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል። ሰላምን ለማጽናት ንግግር እና ውይይት ሁልጊዜም እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን