የአማራ ሳይንት ወረዳ ነዋሪዎች በሰላም እና የጸጥታ ዙሪያ ተወያዩ።

23

ደሴ: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን አማራ ሳይንት ወረዳ የ07 እና 08 ቀበሌ ነዋሪዎች ጽንፈኛው በነዛው የተሳሳተ መረጃ ተታለን የወዳጅ ዘመድ ሕይወት፣ ንብረት እና ልማታችንን አጥተናል ብለዋል። የዘራፊውን ቡድን አሳፋሪ ድርጊት ለማቆም ቆራጥ አቋም በመያዝ መታገል ይገባልም ነው ያሉት።

በመተማመን ላይ የተመሠረተ ትግል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው እና የጽንፈኛውን እኩይ ተግባር በቃ ለማለት ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ከአማራ ሕዝብ እሴት እና ከሰብዓዊነት ያፈነገጡ ግፎች ተፈጽመውብናል ያሉት ነዋሪዎቹ በዚህ ውንብድና የተሰማሩ ልጆች ያሏችሁ ወላጆች የአብራካችሁን ክፋዮች መክራችሁ ከያዙት የጥፋት መንገድ መልሱም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሚፈጸምባቸው ግድያ፣ ዘረፋ እና እገታ መማረራቸውን እና ይህ የግፍ ቁንጮ ቡድን ከነአካቴው እንዲወገድ ለመታገል በተጠንቀቅ መቆማቸውንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። በፋኖ ስም የሚነግደው ቡድን ሕዝቡን በተዛባ መረጃ ማደናገሩ እና እንደ መሸሸጊያ መጠቀሙ በክልሉ የተከሰተው አለመረጋጋት በአጭር ጊዜ እንዲስፋፋ ዕድል እንደሰጠው የተናገሩት የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል ዋና አሥተዳዳሪ አሊ ይማም ናቸው።

ምክትል ዋና አሥተዳዳሪው አኹን ላይ መላ ሕዝቡ የቡድኑን ስውር የዘረፋ ዓላማ ተረድቶ እየታገለው መኾኑንም ገልጸዋል። በአማራ ሳይንት ወረዳ የቤጃ ቀጣና ሕዝብ በቡድኑ ተማሮ በቃ ማለቱን ለማሳያነት አንስተዋል። ጽንፈኛው ቡድን ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ የሚል ቢኾንም ቡድኑ ግን ጨቋኝ እና አረመኔ ነው ያሉት የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል ዋና አሥተዳዳሪ አሊ ይማም ጊዜ ከተሰጠው ከእስካኹኑ የበለጠ ወገኑን ለመግደል፣ ለመዝረፍ እና ለማዋረድ ወደኋላ የማይል መኾኑን ገልጸዋል።

የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች አስመልሳለሁ ብሎ ጫካ የገባው ኀይል በዘረፋ እና በእገታ የግሉን የኢኮኖሚ አቅም እያጠናከረ በአንጻሩ ግን ሕዝብን እያቆረቆዘ መኾኑንም አቶ አሊ ተናግረዋል። ዘራፊ ቡድኑ መንግሥት አልባ ሀገር ለማድረግ ሲፍጨረጨር ቆይቷል፣ የቻለውን ሁሉም አድርጓል ያሉት ምክትል ዋና አሥተዳዳሪው የጽንፈኛው ክፉ ሴራ ሙሉ በሙሉ እንዲከሽፍ ሕዝቡ የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።

በአማራ ሳይንት ወረዳ የቤጃ እና አካባቢው ሕዝብ የቡድኑን የክፋት ዓላማ ተረድቶ ራሱን እና አካባቢውን ለመጠበቅ ያሳየው ተነሳሽነት ለሌሎች አካባቢዎች አስተማሪ ልምድ የሚኾን ነው ያሉት አቶ አሊ የሕዝቡ ወኔ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው የተናገሩት። የዚህን ቡድን እኩይ ሴራ እና ዓላማ በማክሸፍ ሀገርን ከመበተን ሕዝብን ከከፉ እልቂት እና እንግልት ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት የሃይማኖት አባቶች ማገዝ እንዳለባቸውም አቶ አሊ አሳስበዋል።

ሕዝቡ አካባቢውን ነቅቶ ከመጠበቅ ጎን ለጎን በተሳሳተ መረጃ ጫካ የገቡ ልጆቹን መክሮ እንዲመልስ እና የሰላም አማራጭን አንዲከተሉ ማድረግ ይገባዋልም ብለዋል። የአማራ ሳይንት ሕዝብ ያመነበትን የጸና ዓላማ እውን ለማድረግ ወደኋላ የማይል ጀግና ሕዝብ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ ናቸው።

ቡድኑ እታገልለታሁ የሚለው ዓላማ እና የክልሉ መንግሥት የሚያነሳቸው የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው ያሉት ምክትል ኀላፊው እነዚህ ጥያቄዎች የሚመለሱት በሰላማዊ ትግል መኾኑን ተናግረዋል። ቡድኑ ግን የራሱን እኩይ ዓላማ ለማሳካት ሕዝቡን ሲያደናግር መቆየቱን ገልጸዋል።

በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምሥራቅ ዕዝ የ801ኛ ኮር አዛዥ ብርጋደል ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ሕዝቡ የቡድኑን ዕኩይ ዓላማ ተረድቶ የራሱን እና አካባቢውን ሰላም እየጠበቀ መኾኑን ነው የገለጹት። በታጣቂዎች እስካኹን ለተፈጸሙ ጥፋቶች በአካባቢው የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ይቅርታ ማድረጉንም ተናግረዋል።

ለሰላም ጥሪው አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡትን ለመቀበል ዝግጁ መኾናቸውንም አንስተዋል። ሕዝቡ ተደራጅቶ አካባቢውን ለመጠበቅ እያደረገ ያለውን ጥረት ሠራዊቱ በሁለንተናዊ መልኩ ይደግፋልም ብለዋል። ኢትዮጵያ ጸንታ እንድትቀጥል የመከላከያ ሠራዊቱ እንደወትሮው ሁሉ በላቀ የመፈጸም አቅም እና ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የሚተናኮሱትን የውስጥም ኾነ የውጭ ጠላቶችን በመከላከል የሀገራችንን የአሸናፊነት የድል ታሪክ ለማስቀጠል ሠራዊቱ በአስተማማኝ ቁመና ላይ ይገኛልም ነው ያሉት። በሌሎች አካባቢዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ የአማራን ሕዝብ ደኅንነት እና ሰላም ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል በተጠንቀቅ መቆሙንም ብርጋደል ጄኔራሉ አንስተዋል።

ሕዝቡ ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ ማገዝ እንዳለበትም አሳስበዋል። በውይይቱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ከሕዝቡ ተነስተው በሚመለከታቸው የሥራ ኀላፊዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleያለውን ሰላም ለማጽናት እየተሠራ ነው።
Next article“ጊዜው የሃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ምክር ይፈልጋል” አቶ ይርጋ ሲሳይ