ያለውን ሰላም ለማጽናት እየተሠራ ነው።

8

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳደር በመከላከያ ሠራዊት እና በአካባቢው የጸጥታ ኀይሎች ድጋፍ የተገኘውን ሰላም በማስጠበቅ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኛ መኾናቸውን አስታውቀዋል።

የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ጽንፈኛው ቡድን በዞኑ የሰላም ችግር ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተጓደሉ የልማት ሥራዎችን ወደነበሩበት ለመመለስ እና ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ለማድረግ የመከላከያ ሠራዊቱ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

አሥተዳዳሪው ታጣቂው ቡድን እያደረሰ ያለውን ችግር ለሕዝቡ የማሳወቅ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸው በዚህም ምክንያት በዞኑ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በማስፋት እና በማስቀጠል ሕዝቡ ባለቤት እንዲኾን መደረጉን አመልክተዋል።

ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ጽንፈኛው ያደረሰውን ጉዳት እና የዘረፋ ተግባር እንዲኹም የገጠመውን ችግር በአግባቡ እንደተረዳም አብራርተዋል። አኹን ላይ በመከላከያ ሠራዊት እና በአካባቢው የጸጥታ ኀይሎች ድጋፍ የተገኘውን ሰላም ኅብረተሰቡም በእጁ አስገብቶ ወደ ልማት ሊቀይር የሚችልበትን ዕድል ለመፍጠር የሕዝብ ግንኙነት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አሥተዳዳሪው ተናግረዋል።

በዋነኝነት የመኸር እርሻ እና የሰብል እንቅስቃሴ ምቹ ኹኔታ የመፍጠር እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ኾኖ ግብዓት በስፋት ወደ አርሶ አደሮች እንዲገባ የመንገድ ደኅንነት ሥራዎች መሠራታቸውን አቶ ኑርልኝ ጠቅሰዋል። የጤና እና የትምህርት ሥራዎችንም ባለሙያዎች ተረጋግተው እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል።

በሠራዊቱ እና በዞኑ የጸጥታ ኀይል እየተሠራ ያለው ሕግ የማስከበር ሥራ ጽንፈኛው እያደረሰ ያለውን እና ለማድረስ የተዘጋጀበትን እኩይ ተግባር ከማምከን ባሻገር ሕዝቡ በዘላቂነት ባለቤት በመኾን ልማቱን እያፋጠነ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።

ማኅበረሰቡ እና የአካባቢው የጸጥታ መዋቅር ራሱን ለመቻል እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱንም ነው የገለጹት። ማኅበረሰቡ የጀመረውን በራስ አቅም የአካባቢውን ሰላም የማጠናከር እና የማስቀጠል ተግባር መስፋት እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት። መሪዎች እና ሕዝቡ ከጸጥታ አካላቱ ጋር በቅንጅት መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።

አቶ ኑርልኝ በማወቅም ኾነ ባለማወቅ ወደ ጫካ ለገቡ ጽንፈኞች ጊዜው ሳይረፍድ የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ለጸጥታ ኀይሉ እጃቸውን እንዲሰጡ እና ወደ ቀያቸው እንዲገቡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ እና ልማትን በላቀ ደረጃ ለማፋጠን ወሳኝ ሚና ለተጫወተው የመከላከያ ሠራዊት ምሥጋና አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleመምህራን በወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ነው።
Next articleየአማራ ሳይንት ወረዳ ነዋሪዎች በሰላም እና የጸጥታ ዙሪያ ተወያዩ።