ትኩረት የሚያሻው የፀረ-ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም።

24

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በግብርናው ዘርፍ ለተለያዩ አገልግሎቶች አርሶ አደሮች የሚጠቀሟቸው ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች አያያዝ፣ አጠቃቀም እና አወጋገድ ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ፀረ-ተባይ ማለት የሰውን እና የእንስሳትን በሽታ አስተላላፊዎችን ጨምሮ ማንኛውንም ተባይ ለመከላከል፣ ለማጥፋት እና ለመቆጣጠር የሚያገለግል ማንኛውም ንጥረ ነገር ወይም የንጥረ ነገሮች ድብልቅ ሲኾን በእፅዋት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚያገለግል ነው፡፡

እነዚህን ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰብሎች ላይ ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር ሲባል አርሶ አደሩ በስፋት እየተጠቀማቸው ይገኛል፡፡ በመንግሥትም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ጥራት ያላቸው ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች እንዲመረቱ፣ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተሠራ ይገኛል፡፡

አርሶ አደሮች የሚጠቀሟቸው ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች አያያዝ፣ አጠቃቀም እና አወጋገድ ላይ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ይመከራል፡፡ በተለይም አኹን የያዝነው የእርሻ ወቅት እንደመኾኑ መጠን አርሶ አደሮች በቀጣይ የተለያዩ ኬሚካሎችን በስፋት እንደሚጠቀሙ ይታወቃል፡፡ ኾኖም የእነዚህ ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች አያያዝ፣ አጠቃቀም እና አወጋገድ ምን መኾን አለበት የሚለውን የባለሙያዎችን ምክረ ሀሳብ ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የእፅዋት ጥበቃ ባለሙያ አበበ አናጋው እንደገለጹልን ፀረ-ተባይ ኬሚካል ማለት ፀረ-ሰብል ተባዮችን ለመከላከል ወይም ለማስወገድ የምንጠቀምበት መድኃኒት ወይም መርዝ ነው፡፡ መርዝነቱ ለአካባቢ፣ ለሰው ልጅ፣ ለእንስሳትና ለተባዮች ጉዳት በማድረስ የሚገለጽ ነው፡፡ ነገር ግን ጠቀሜታውን በመውሰድ በማሳ ላይ ሰብሎች እና በጎተራ ውስጥ ምርትን የሚያበላሹ ተባዮችን ለመከላከል ስለምንጠቀምበት ፀረ-ተባይ ተብሎ ይጠራል ብለዋል፡፡

እንደባለሙያው ገለጻ እነዚህ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ ሲውሉ ከርጭት በፊት፣ በርጭት ወቅት እና ከርጭት በኋላ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች እንዳሉ ነው የተናገሩት፡፡ ከርጭት በፊት ኬሚካሉን የምንገዛው ለምንድን ነው? የሚለው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ፀረ-ሰብል ተባይ ተከስቶ ከኾነ ለተከሰተው ተባይ ተገቢ የኾነ ኬሚካል መኾኑን ባለሙያ በማማከር ከሚመለከተው ሕጋዊ አካል መገዛት አለበት፡፡

ከተገዛ በኋላ ወደ ቤት ሲመጣ ሰዎችን፣ እንስሳትን እና አካባቢን ለብክለት ተጋላጭ በማያደርግ መልኩ መያዝ እና መቀመጥ አለበት ብለዋል፡፡ በአግባቡ ካልተያዘ በሰዎች፣ በእንስሳት እና በአካባቢ ላይ ብክለት እና ጉዳት ስለሚያስከትል ጥንቃቄ ማድረግ እና ከሚጠቀመው ሰው ውጭ ሌሎች ሰዎች በማይደርሱበት ሁኔታ መቀመጥ አለበት፡፡

የኬሚካል ማሸጊያው የተቀደደ አለመኾኑንም ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት፡፡ ወደ ርጭት ሲገባ ኬሚካሉን የሚረጨው ሰው በኬሚካል ጉዳት እንዳይደርስበት ተገቢ የኾነ ሙሉ አካሉን ሊሸፍን የሚችል አልባሳት መልበስ አለበት፡፡ አለባበሱ ራሱን ችሎ ሂደት ስላለው ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር መተግበር እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

ኬሚካሉን የሚረጨው ሰው የሚጠቀመው ልብስ ለዚህ አገልግሎት ብቻ የሚውል መኾን እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ኬሚካሉን ለመርጨት የሚጠቀሙበትን የመርጫ መሳሪያ ለየትኛው ኬሚካል የትኛውን መጠቀም እንዳለባቸው ማወቅ እና መለየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የመርጫ መሳሪያዎች ለተለያዩ ኬሚካሎች የተለያየ የቀዳዳ ስፋት ያለውን መርጫ መሳሪያ ለይቶ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ለተባይ እና ለአረም የምንጠቀመው የተለያየ ነው፡፡ ከባለሙያ ጋር በመነጋገር መሳሪያው ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጥም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

አብዛኞቹ ኬሚካሎች በውኃ ተበጥብጠው የሚረጩ በመኾናቸው ንጹህ እና በቂ ውኃ መኖሩን መረጋገጥ አለበት፡፡ ይህ ከተሟላ በኋላ የሚረጨው ኬሚካል ለአንድ ሄክታር ምን ያህል ኬሚካል ያስፈልጋል? የሚረጨው ማሳ ምን ያህል ነው? የሚለው ከባለሙያ ጋር በመነጋገር ተሰልቶ ምን ያህል መጠቀም እንዳለባቸው መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡

በርጭት ወቅት ሌላው ትኩረት የሚፈልገው ነገር የነፋስ አቅጣጫ ነው፡፡ ርጭቱ ከነፋስ መነሻ በኩል ቢጀመር በነፋሱ መጨረሻ እንዲያልቅ ይደረጋል፡፡ በዚህ ጊዜ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ የሚረጨውን ሰው፣ በዙሪያ ያሉ ሰዎች እና እንስሳት እንዲሁም አካባቢን ለብክለት እንደሚዳርግ ጠቁመዋል፡፡

ከርጭት በኋላ ጉድጓድ ቆፍረው የተጠቀሙበትን መሳሪያ መርጫውን በደንብ በማጠብ የኬሚካሉን ቅሪት በውኃ አጥበው መቅበር አለባቸው፡፡ የረጨው ሰው ከቤተሰቦቹ ጋር ከመቀላቀሉ በፊት ሰውነቱን በሚገባ መታጠብ እና የለበሰው ልብስም በደንብ መታጠብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ምንም እንኳን ይላሉ አቶ አበበ ለአርሶ አደሩ የፀረ-ተባይ ኬሚካል አያያዝ፣ አጠቃቀም እና አወጋገድ ድጋፍ በባለሙያዎች የሚደረግ ቢኾንም በአርሶ አደሮች ዘንድ አልፎ አልፎ በትክክል ተግባራዊ በማድረግ በኩል ክፍተቶች ይታያሉ፡፡

ጥንቃቄዎችን ትኩረት ሰጥቶ አለመተግበር ደግሞ በጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ ጉዳቱም ወዲያው የሚታየው ኬሚካሉ ሲረጭ እንደየ ኬሚካሉ ባህሪ ሰውነታቸውን ሲነካቸው የማቃጠል፣ የመዝለፍለፍ ከፍ ሲልም የማስመለስ ሁኔታዎች ያጋጥማሉ፡፡

ኬሚካል ሲረጭ በአካባቢው በነፋስ አማካኝነት ወደ ሕጻናት ሲደርስ ሰውነታቸውን ለረጅም ሰዓት እንደሚያቃጥላቸው በተግባር የተስተዋለ ጉዳይ እንደኾነም አንስተዋል፡፡

ኬሚካል በረጅም ጊዜም አስፈላጊው ጥንቃቄ በማድረግ የጎንዮሽ ጉዳቱን መቀነስ ካልተቻለ ለተለያዩ በሽታዎች የሚያጋልጥ መኾኑን ይገልጻሉ፡፡

ስለዚህ ኬሚካሉ ጥቅም ላይ ሲውል ከላይ የተጠቀሱ መሰረታዊ ጉዳዮች በአርሶ አደሮች ዘንድ ተግባራዊ ከተደረገ እና በአግባቡ ከተጠቀሙ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ እንደሚቻል ነው አቶ አበበ የገለጹልን፡፡

ዘጋቢ፡ ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሚዲያ አጋጣሚዎችን ሁሉ በመጠቀም ለዘላቂ መፍትሄ መሥራት ይጠበቅበታል።
Next articleየፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መያዣ መንገዶች ፦