ሚዲያ አጋጣሚዎችን ሁሉ በመጠቀም ለዘላቂ መፍትሄ መሥራት ይጠበቅበታል።

12

ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሠራተኞች ”በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ሚና እና የቀጣይ አቅጣጫዎች” በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ተወያይተዋል። የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ነባራዊ ሁኔታ ለሀገር ዕድገት ያለው ሚና፣ ተግዳሮቶች እና የማኅበራዊ ሚዲያ አፍራሽ ክስተቶች በውይይቱ ላይ ተነስተዋል።

ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የተገኙ ስኬቶች፣ ፈተናዎች እና መፍትሄዎችም በሰነዱ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ሚዲያው ለጋራ ትርክት ግንባታ እና ሀገራዊ መግባባት መሥራት አለበት። ሕዝብ የተማረረባቸውን ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለማስተካከልም ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተነስቷል።

ተወያዩቹ በክልሉ ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ አሉ ያሏቸውን ውስንነቶች እና የመፍትሄ ሃሳቦች አንስተዋል። በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካባቢ የሚስተዋሉ ችግሮች ተገልጋዩን ማኅበረሰብ የሚያማርሩ ኾነዋል ያሉት ተወያዩቹ ሕገ ወጥ አሰራሮች ባሕል ከሚኾኑበት ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ለመፍትሄዎቹ መረባረብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ተወያዮቹ አገልግሎት አሰጣጡን ፈትሾ ለሕዝብ ለማሳወቅ እና ሁሉም የመፍትሄው አካል ኾኖ እንዲረባረብ ለማድረግ የመረጃ ሰጪዎች ፈቃደኛ አለመኾን መሰናክል እንደኾነባቸው አንስተዋል። ሚዲያ ዜጎችን የማስረዳት፣ ለመልካም አሥተዳደር እና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መስፈን መሥራት አለበት ያሉት የአሚኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ ናቸው።

ሚዲያ የማኅበረሰብ አስተሳሰብን የመቅረጽ፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን የማስፋት፣ ልማትን የመደገፍ፣ ለድምጽ አልባዎች ድምጽ የመኾን እና የሀገር ገጽታ የመገንባት ኀላፊነት አለበት ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አሚኮም በተሰጠው ኀላፊነት ልክ ለኅብረተሰብ ለውጥ መትጋት ይኖርበታል ብለዋል።

ውይይቱን የመሩት የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) የክልሉ መሠረታዊ ችግሮች ቀደም ተብሎ የተሠራባቸው እንደነበሩ ገልጸዋል። መሪዎችን ባጎደሉት ነገር ሁሉ መጠየቅ ከሚዲያው ይጠበቃል ያሉት ዶክተር መንገሻ የሚስተዋሉ ጅምር ስኬቶችንም እውቅና መስጠት እና ሕዝብን ማስተባበር ይጠበቃል ነው ያሉት።

ሚዲያው ብልሹ አሠራር ባሕል እንዳይኾን መታገል እና የሕዝብን ችግር የመፍታት አደራ አለበት ያሉት ዶክተር መንገሻ የጋራ ዕቅድ አውጥተን በጋራ እንሠራለን ነው ያሉት።

የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በመገንዘብ ተወዳዳሪ ክልል እንዲኾን መሥራት እንደሚገባው አንስተዋል። በአማራ ሕዝብ ዘላቂ ጥቅሞች ዙሪያ በትጋት መሥራት ይጠበቃል ያሉት ዶክተር መንገሻ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መሥራት ከሚዲያው እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ በጎንደር ከተማ የተገነባውን ቲቲኬ የዘይት ፋብሪካ መረቁ።
Next articleትኩረት የሚያሻው የፀረ-ተባይ ኬሚካል አጠቃቀም።